ኢትዮጵያ በበርካታ የተፈጥሮ ሃብቶች የታደለች ሀገር ናት። ሆኖም ግን ሳትጠቀምባቸው ለዘመናት በመቆየቷ በርካቶች በድህነት ውስጥ ናቸው። ያላት የተፈጥሮ ሃብት ከራሷ አልፎ ለጎረቤቶቿም የሚተርፍ ቢሆንም፣ በአግባቡ ጥቅም ላይ ሳይውል ቆይቷል።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ ሳትጠቀምባቸው የቆዩትን የተፈጥሮ ሃብቶቿን ለመጠቀም የሚያስችል ጉዞ መጀመሯ የሚበረታ እና መጠናከር ያለበት መሆኑን የምጣኔ ሃብት ባለሙያዎች ይገልፃሉ።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሃብቶች የታደለች፣ በወጣት ኃይል የተሞላች ብትሆንም ከሌሎች ሀገራት አንፃር ወደ ኋላ መቅረታችን በቁጭት እንድንሰራ ያነሳሳል የሚሉት በወራቤ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት መምህርና ተመራማሪ የሆኑት መሐመድ ኢሣ (ዶ/ር) ናቸው።
አሁን ላይ በተፈጥሮ ጋዝ፣ በቱሪዝም፣ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት እና በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሚታዩ ተስፋ ሰጪ ግዙፍ ፕሮጀክቶች በተፈጥሮ ሃብታችን በስፋት መጠቀም እንደምንችል ያሳዩ ናቸው ሲሉም ጠቁመዋል።
በቀጣይም ሀገራዊ ልማትን የሚያሳድጉ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ነው የተናገሩት።
የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ከፍተኛ አማካሪ የሆኑት አሰፋ ሱሞሮ በበኩላቸው፣ ያልተጠቀምንባቸውን ዘመናት ለማካካስ በቁጭትና በእልህ የጀመርነው የልማት ጉዞ መጠናከር አለበት ብለዋል።
የሀገር ብልፅግና ለግለሰብም የሚተርፍ እድገትን እንደሚያመጣ እንደ ቻይና ያሉ ሀገራት ምሳሌ መሆናቸውን ጠቁመው፤ እያንዳንዱ ዜጋ ለሀገሩ ዕድገት ከመንግሥት ጋር ተባብሮ መሥራት እንደሚጠበቅበትም አብራርተዋል።
በስፋት ያልተጠቀምንባቸውን የቱሪዝም፣ የማዕድን እና የተለያዩ የተፈጥሮ ሃብቶችን በማልማት የተሻለች ሀገር ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት መደገፍ እንደሚገባም አመላክተዋል።
በሜሮን ንብረት