Search

የኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ህዳር 21 ይከበራል

ማክሰኞ ኅዳር 02, 2018 296

የኢፌዴሪ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት ክብረ በዓልን አስመልክቶ የአየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄኔራል ይልማ መርዳሳ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሌ/ጄኔራል ይልማ መርዳሳ በመግለጫቸው፤ ኢትዮጵያ እንደ አየር ኃይል ያሉ ዘመናዊ ተቋማት ከገነቡ ሀገራት አንዷ ነች ብለዋል።

ኢትዮጵያ ጥንታዊ ሀገር ናት ያሉት ሌ/ጄኔራል ይልማ መርዳሳ፤ ከአፍሪካ ቀድማ ዘመናዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን የገነባች ሀገር መሆኗን ገልፀዋል።

ከእነዚህ ተቋማት መካከል የኢፌዴሪ አየር ኃይል አንዱ መሆኑን ጠቁመው፤ ተቋሙ እራሱን በሰው ሀይል፣ በውጊያ መሰረተ ልማት እና በሌሎች ዘርፎች እያጠናከረ ነው ብለዋል።

የዘንድሮ 90ኛ የአየር ኃይሉ የምስረታ በዓል ህዳር 21 ቀን በተለያዩ መርኃ ግብሮች በድምቀት እንደሚከበር ሌ/ጀነራል ይልማ መርዳሳ ገልጸዋል።

የምስረታ በዓሉ በተለያዩ ሁነቶች እና ትርዒቶች እንደሚከበርም ጠቅሰዋል።

የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግም ህዳር 21 "ለአየር ኃይል ዕድገት በሙሉ አቅሜ እሮጣለሁ" በሚል ሀሳብ በቢሾፍቱ ከተማ የ10 ኪ.ሜ ዓለምአቀፍ የጎዳና ሩጫ ይካሄዳል ተብሏል።

በመግለጫው የተገኙት የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አለማየሁ አሰፋ፤ የሩጫ ውድድሩ ጨምሮ ሌሎች ሁነቶች ለከተማዋ ገጽታ እና እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኮማንደር ስለሺ ስህን በበኩላቸው፤ በዚህ የጎዳና ሩጫ ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡ ተሳታፊዎች ጨምሮ ከ25ሺ በላይ ሰዎች ይሳተፉበታል ብለዋል።

ይህ የጎዳና ላይ ሩጫ በቢሾፍቱ በቋሚነት እንደሚዘጋጅም ተጠቅሷል።

በአባዲ ወይናይ

#ebc #ebcdotstream #Ethiopia #AirForce