20ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ኢትዮጵያውያን በሀገራዊ አጀንዳዎች ላይ በጋራ በቆምንበት ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ ላይ ሆነን የምናከብረው በመሆኑ ልዩ ይሆናል ሲሉ በፌድሬሽን ምክር ቤት የመንግሥት ግንኙነት፣ የዴሞክራሲ አንድነት እና የሕገ-መንግሥት አስተምህሮ ቋሚ ኮሚቴ ፀሐፊ ወ/ሮ ባንቺይርጋ መለሰ ተናገሩ።
የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን ባለፉት 19 ዓመታት ሲከበር የሕዝቦችን ትሥሥር በማጎልበት፣ የክልሎች የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን ለማሳደግ፣ የቱሪዝም መሠረተ ልማቶችን ማልማት እና ማስተዋወቅ ላይ የጎላ አስተዋፅኦ እንደነበረውም ተናግረዋል።
ከአጎራባች ሀገራት ጋር የዲፕሎማሲ ግንኙነትን ማጠናከር እና የሀገር ገፅታ ግንባታ ላይም አስተውፅኦው ከፍተኛ እንደሆነም ወ/ሮ ባንቺይርጋ መለሰ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ወደ አዲስ ምዕራፍ በመሻገር ሂደት ውስጥ በዓሉ በሕዝቦች መካከል ሀገራዊ መግባባት እንዲፈጠር፣ ዲሞክራሲያዊ አንድነት እንዲጠናከር እና ኅብረብሔራዊ አንድነት እንዲጎለብት የሚያስችሉ ተግባራት የሚከወንበት በዓል መሆኑንም ተናግረዋል።
በዓሉ በሁሉም ክልሎች መከበሩ የጋራ መግባባት እንዲጠናክር እያደረገ ሲሆን ዘንድሮም በኤምባሲዎች፣ በዩኒቨርሲቲዎች በተለያዩ ሥነ-ሥርዓቶች የሕዝቦችን ትሥሥር በሚያጠናክር መልኩ ይከበራል።
20ኛው የብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ ኅዳር 29 ቀን 2018 ዓ.ም “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለኅብረብሔራዊ መግባባት'' በሚል መሪ ቃል ይከበራል።
ይህንኑ በዓል ለማክበር በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሆሳዕና ዝግጅት መጠናቀቁ ተገልጿል።
በሃይማኖት ከበደ