ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉባኤ ኮፕ32ን እንድታስተናግድ የአፍሪካ ተደራዳሪዎች ቡድን ድጋፉን መስጠቱ ይታወቃል።
በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል የአፍሪካ ተደራዳሪዎች ቡድን ሊቀመንበር የሆኑት ሪቻርድ ሙዩንጊ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ኮፕ32 ለማዘጋጀት ትክክልኛዋ ሀገር መሆኗን ጠቁመዋል።
"ኢትዮጵያ ጉባኤውን ማዘጋጀቷ የአፍሪካ ተደራዳሪዎች ቡድን ምርጫ ነው” ሲሉም ሪቻርድ ሙዩንጊ (ዶ/ር) ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።
በብራዚል ቤሌም ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የተመድ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ኮፕ30 ላይ የብራዚሉ ፕሬዚዳንት ሉላ ዳ ሲልቫ እ.አ.አ በ2027 የሚከናወነውን ጉባኤ አስተናጋጅነት በተመለከተ የአፍሪካ ሀገራት ምርጫቸው ኢትዮጵያ መሆኗን አረጋግጠዋል።
"የኢትዮጵያን የጉባኤው አስተናጋጅነትን በደስታ እንደሚቀበሉት እና በአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ረገድ በአፍሪካ ያላትን የመሪነት ሚና በበጎ እንደሚመለከቱት የገለጹት ደግሞ “350.org” የተሰኘው ግብረ-ሰናይ ድርጅት የአፍሪካ ከፍተኛ አስተባባሪ ሩኪያ ካሚስ ናቸው።

የተመድ ዓመታዊው የአየር ንብረት ጉባኤ በየአህጉራቱ በዙር የሚከናወን ሲሆን፤ ዘንድሮ ብራዚል የላቲን አሜሪካ እና የካሪቢያን ግዛቶችን በመወከል ኮፕ30ን እያስተናገደች ትገኛለች።
አፍሪካ ጉባኤውን እ.አ.እ በ2027 የምታስተናግድ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ ለአስተናጋጅነት ተፎካካሪ የነበረችውን ናይጄሪያን በመብለጥ በአፍሪካውያን ዘንድ ተመራጭ ሆናለች።
እየተካሄደ በሚገኘው የኮፕ30 ጉባኤ ማጠናቀቂያ ላይም ኢትዮጵያ ኮፕ32 እንድታዘጋጅ ሙሉ ድጋፍ ታገኛለች ተብሎ ይጠበቃል።
በጌትነት ተስፋማርያም