የፓን አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ የሆነው እና በማኅበራዊ ሚዲያ ስለ አፍሪካ መልካም ገጽታ የሚሰራው በርትሆልድ ኮቢ ዊንክለር አኮን ወይም በማኅበራዊ ሚዲያ ሥራዎቹ ዎዴ ማያ በመባል የሚታወቀው ጋናዊ ሀገር አሳሽ፤ ስለ ዓድዋ ድል ሲገልፅ በታሪክ ውስጥ እየሄድኩ ስለሆነ ታሪክ እየሰራሁ እንደሆነ ይሰማኛል ብሏል።
ኢትዮጵያ በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ካልተያዙት ሁለት አፍሪካውያን ሀገራት አንዷ መሆኗን በማስታወስ ነው ስለዓድዋ የሚያትተውን ትረካውን የሚጀምረው ማያ።
ወደ ዓድዋ ተራሮች ጉዞ እያደረገም፣ "ይህን ጉዞ ሳደርግ በጣም ልዩ ስሜት እየተሰማኝ ነው፤ ምክንያቱም እየሄድኩ ያለሁት ወደ የአፍሪካ የነፃነት ቤት ነውና" ይላል።
ዓድዋ አፍሪካውያን አፍሪካን ልትቀራመት የመጣችውን ጣሊያን ድል የነሱበት ቦታ ነው በማለት የዓድዋን ከፍታ የሚገልጸው ዎዴ ማያ፣ ሁሉም አፍሪካውያን ይህን የነፃነታቸውን ምድር ማየት እንዳለባቸው ይጠቁማል።

የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም የዓለምን ታሪክ የለወጠ ክስተት እንደተፈጸመ የሚገልጸው ማያ፣ ያ ታሪክ ደግሞ በትክክል የተፈጸመው እዚህ ነው በማለት የዓድዋን ምድር ይጠቅሳል።
ዓድዋ ኢትዮጵያውያን እንደ አንድ ተዋህደው አስደናቂ ታሪክ እንደሰሩበት ጠቅሶ፣ ዓላማቸውም ቅኝ ገዢዎችን በማሸነፍ ነፃነታቸውን መጠበቅ እንደነበር ያብራራል።
የመጀመሪያው ጦርነት የተጀመረው ምንድብድብ በተባለው ቦታ እንደሆነ የሚገልጹት የቦታው አስጎብኚ፣ ጄኔራል ባራቲየሪ የሚመሩት የጣሊያን ጦር በአራት ግንባሮች ተሰልፈው ወደ ጦርነቱ መግባታቸውን ጠቅሰዋል።
ታላቁ የአፍሪካ ጄኔራል ራስ አሉላ ለዓድዋ ድል ታላቅ አስተዋጽኦ ካደረጉት ጀግኖች መካከል ግንባር ቀደሙ እንደሆኑ ዎዴ ማያ አንስቷል።

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የጦር ዘማቾችን እየመሩ ከአዲስ አበባ እስከ ዓድዋ የተደረገው ጉዞ ሰባት ወራት ገደማ መውሰዱን የሚያስታውሰው ማያ፣ ተጨማሪ ዘማቾችም በየመንገዱ እየተቀላቀሏቸው እስከ ውጊያው ቦታ እንደደረሱ ይጠቁማል።
አውሮፓውያን አፍሪካን ሲቀራመቱ ቋንቋቸውንም እንደቀየሩባቸው ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ጣሊያንኛ ሳይሆን የራሳቸውን ቋንቋ እና ባህል ይዘው የቆዩት ለነፃነታቸው ባደረጉት ትግል እና ባገኙት ድል እንደሆነም ያብራራል አሳሹ።
ኢትዮጵያውያን ለነፃነት የተዋደቁባቸው የዓድዋ ተራሮች የመላው አፍሪካ መንፈስ ያለበት መሆኑንም በአድናቆት ይገልጻል።
አፍሪካውያን ሙሉ በሙሉ ነፃነታቸውን እስከሚቀዳጁ ድረስ በዓድዋ ድል መንፈስ መንቀሳቀስ እንዳለባቸውም ያሳስባል።

የየትኛውም ጥቁር አፍሪካዊ ምኞት ነፃነቱ እንደሆነ የሚጠቅሰው ማያ፣ በዚያ የነፃነት ምኞት የተገኘው ድል ከዓድዋ እንደተጀመረ ይናገራል።
ኢትዮጵያውያን በዓድዋ ለራሳቸው እና በቅኝ ግዛት ስር ለነበሩ ሕዝቦች ነፃነት በመዋደቃቸው የፓን አፍሪካኒዝም መንፈስ በዓድዋ መወለዱን ገልጿል።
"እናም ኢትዮጵያውያን የነፃነት ቀንን ሳይሆን የድል ቀንን የሚያከብሩት በዓድዋ ላይ በተቀዳጁት አስደናቂ ድል ምክንያት ነው" ይላል ማያ።
ይህ የአፍሪካውያን እና የጥቁር ሕዝቦች ድል ጋናን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የሰንደቅ አላማዎቻቸውን ቀለማት ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ እንዲወስዱ እንዳደረጋቸውም ጠቅሷል።
በለሚ ታደሰ