ኢትዮጵያ 32ኛውን የአለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ እንድታዘጋጅ መመረጧ እየወሰደቻቸው ያሉ ተግባራዊ እርምጃዎች ውጤት ማሳየታቸውን ያመለክታል ሲሉ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
በብራዚል ቤሌም እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የኢትዮጵያን መመረጥ አስመልክቶ ከኢቢሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ መመረጥ እጅግ ደስ ያሰኛል፤ መላው ኢትዮጵያውያንን እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ ብለዋል።
በተለይ አፍሪካውያን ወንድሞች ያሳዩት ድጋፍ የሚደነቅና በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን እምነት በድጋሜ ያረጋገጡበት ነው ያሉት ሚኒስትሯ፤ የቀረው መደበኛ ስርዓቱን ጠብቆ መፅደቁ ብቻ በመሆኑ ትልቅ ስኬት ነው ሲሉ ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በትክክል መንግስት ከህዝብ ጋር ተባብሮ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ተግባራዊ እርምጃ እየወሰደች መሆኗን በተግባር ያረጋገጠ መሆኑንም ተናግረዋል።
2ኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በስኬት ማዘጋጀቷ አቅሟን ያሳየ እና ያስመሰከረ መሆኑ ትልልቅ አለም አቀፍ ኮንፈረንሶች በብቃት ማስተናገዷ እንድትመረጥ አስተዋፅኦ አድርጓል ብለዋል።
ጉባኤው የሀገራችንን የዲፕሎማሲ አቅም የሚጨምር የሚያስገኘውም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳ ከፍ ያለ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሰራናቸው ስራዎች ዓለም መመስከር መጀሩ መሳያ ነው ሲሉ ጠቁመዋል።
ተለዋዋጭ በሆነው ዓለም ሀገራት የአየር ንብረጥ ለውጥ ጉዳይን ትኩረት አድርገው ለተግባራዊ እርምጃዎች እንዲፈጥኑ ብሎም የአየር ንብረት ለውጥን የመከላከል የገንዘብ ድጋፍ ምቹ ሁኔታዎች መኖራቸውን ለማሳመን ትልቅ እድል የሚሰጠን ይሆናል ነው ያሉት።
ሚኒስትሯ በብራዚል ቤሌም ጉባኤም ኢትዮጵያ ባዘጋጀችው እልፍኝ (ፓቪሊዮን) የኢትዮጵያን የአየር ንብረት ለውጥ የመፍትሄ እርምጃዎችን ከሚደግፉ እና አብረው ከሚሰሩ ኖርዌይ እና ኔዘርላንድ ሀገራት ተወካዮች ጋር ውይይት አድርገናል ብለዋል።
እንዲሁም ከወቅቱ የአፍሪካ ቡድን የወቅቱ ሊቀመንበር ከነበረችው ታንዛንያ ተወካዬች ጋር ተነጋግረን ኢትዮጵያ እንድትመረጥ ለነበራቸው ድጋፍም ምስጋና አቅርበናል ብለዋል።
ሀገራቱ ኢትዮጵያ በርግጥም ይህንን ጉባኤ በስኬት እንደምታስተናግደው ሙሉ እምነት እንዳላቸው እና ተገቢ ምርጫ መሆኑንም አንስተዋል ነው ያሉት።
ከ15 በላይ የጎንዮሽ ውይይት እና ምክክሮች በቀጣይ ቀናት እንደሚጠበቁ ያነሱት ሚኒስትሯ፤ የኢትዮጵያን ተግባራዊ ስራዎች ለማስተዋወቅ ትልቅ እድል በመሆኑ ሰፊ ስራ ይጠበቃል፣ ተጨማሪ የልማት አጋርነት እና ፋይናንስ ለማሰባሰብም የምንሰራበት ይሆናል ብለዋል።
በሀብታሙ ተክለሥላሴ
#ebcdotstream #Ethiopia #COP30 #africa