ብሔራዊ ጥቅም ለአንድ የፖለቲካ ፓርቲ ብቻ የሚተው ጉዳይ አይደለም ሲሉ የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ገለጹ፡፡
የነጻነት እና እኩልነት ፓርቲ የህዝብ ግኑኝነት ኃላፊ ነቢሃ መሐመድ ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የሀገራችን ጥቅም የማስጠበቅና የማስከበር ስራ ለገዢው ፓርቲ ብቻ የሚተው ጉዳይ አይደለም ብለዋል፡፡
የባህር ብር ጉዳይ አሁን ላይ መነሳቱ አስፈላጊ አንደሆነ ገልፀው፤ ያጣንባቸው ዓመታት ያስቆጫሉ ነው ያሉት፡፡
የቦሩ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ የውጭ እና ዓለም አቀፋ ግኑኝነት ኃላፊ መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ሰላም እና እድገት የሚመኝ ሁሉ ለብሔራዊ ጥቅሟ መሳካት የበኩሉን ጥረት ማድረግ አለበት ብለዋል፡፡
የፖለቲካ ልዩነቶች ቢኖሩ እንኳን የሀገር ጉዳይ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ እንደሚሰጠውም ነው የገለጹት፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ላለች ትልቅ እና የህዝብ ብዛቷ ከፍተኛ ለሆነ ሀገር በልኳ የባህር በር ሊኖራት ይገባል ነው ያሉት፡፡
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግኑኝነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል ፈቲሂ ማህዲ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ለ30 ዓመታት ያክል ታፍና እንደቆየች አንስተው፤ አሁን ላይ ግን የቀይ ባህር ጉዳይ አጀንዳ ሆኖ የህዝብ ጥያቄ ሆኖ ተነስቷል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ብሔራዊ ጥቅም ሁሉንም የሀገሪቱን ነዋሪዎች የሚያጠቃልል እንደሆነም አመልክተዋል፡፡
ምሁራን፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ በባህር በር ያሉ የሀገሪቱ ብሔራዊ ጥቅሞች ላይ የማይዛነፍ ወጥ አቋም ሊኖረው እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡
በሜሮን ንብረት
#Ebc #Ebcdotstream #Ethiopia #national_interest #seaaccess