የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ከአዘርባጃን ኮፕ 29 ፕሬዝዳንት ሙክታር ባበዬቭ ጋር ተወያይተዋል።
በብራዚል ቤሌም እየተካሄደ በሚገኘው የዓለም አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ የጎንዬሽ ውይይት ነው ሚኒስትሯ ከፕሬዝደንቱ ጋር የተወያዩት።
ኮፕ 29ን በስኬት ያስተናገደችው አዘርባጃን የመርኃ ግብሩ ፕሬዝደንት የነበሩት ሙክታር ባባዬቭ፤ ኢትዮጵያ ኮፕ 32ን ለማዘጋጀት በመመረጧ ተደስተናል፣ እንደምታሳካውም እንተማመናለን ብለዋል።
አዲስ አበባ እጅግ እያማረባት እና እያደገች ያለች ከተማ መሆኗን እናውቃለን ያሉት ፕሬዝደንቱ፤ ከተማዋ የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗንና ስኬታማ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን እያስተናገደች እንደምትገኝ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከሁሉ በላይ የአፍሪካ ኩራት በሆነው አየር መንገዷ እንግዳ ለመቀበል የማትቸገር ሀገር በመሆኗ መመረጧ አስደስቶናል ሲሉም ነው ከውይይታቸው በኋላ ለኢቢሲ የተናገሩት።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም፤ ኢትዮጵያ ዝግጅቱን በማሰናዳት ሂደት ከጎኗ በመቆም ሁለንተናዊ ድጋፍ ለማድረግም ዝግጁ ነን ብለዋል።
የፕላን እና ልማት ሚኒስትሯ ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)፤ ለኮፕ 32 ከወዲሁ ለሚደረገው ዝግጅት ከአዘርባጃን ኮፕ ፕሬዝደንት ጋር የተደረገው ውይይት እጅጉን ጠቃሚ እና ልምድ ለመውሰድ በር ከፋች መሆኑን ገልፀዋል።
ሀገራቱ ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው እንደመሆናቸው የአዘርባጃን ከኢትዮጵያ ጎን መቆምና ድጋፍ ለማድረግም ቀና ሀሳባቸውን መግለፅ ጉዟችን የሰመረ እንዲሆን የራሱ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል።
የአዘርባጃን ኮፕ እጅግ ስኬታማ ከሚባሉት መካከል እንደነበር ያነሱት ሚኒስትሯ፤ ከሀገሪቱ ልምድ በመውሰድ ኢትዮጵያ የምታዘጋጀው ኮፕ 32 በብዙ መንገድ የላቀ እንዲሆን የሚያግዝ ፍሬያማ ውይይት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
በሀብታሙ ተክለስላሴ
#Ebc #Ebcdotstream #Ethiopia #COP30 #COP32 #ClimateChange