Search

10ኛው የአፍሪካ ሕብረት-ተመድ የጋራ ዓመታዊ ኮንፈረንስ በአዲስ አበባ ይካሄዳል

ሓሙስ ኅዳር 04, 2018 148

2026 የሚካሄደውን 10ኛውን የአፍሪካ ሕብረት-ተመድ ዓመታዊ ኮንፈረንስ አዲስ አበባ እንደምታስተናግድ ተገለጸ።

የአፍሪካ ሕብረት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም፣ የደኅንነት እና የዘላቂ ልማት አጋርነታቸውን የበለጠ ለማጠናከር ተስማምተዋል።

9ኛው የአፍሪካ ሕብረት-የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዓመታዊ ኮንፈረንስ ኒው ዮርክ በሚገኘው የድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት እየተካሄደ ይገኛል።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ማህሙድ አሊ ዩሱፍ እና የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ኮንፈረንሱን በጋራ መርተዋል።

መሪዎቹ በአፍሪካ ሕብረት እና በተመድ መካከል ያለው ዘላቂ አጋርነት ለዓለም አቀፍ ሰላም፣ ደኅንነት እና ዘላቂ ልማት የማዕዘን ድንጋይ መሆኑን አረጋግጠዋል።

የትጥቅ ግጭቶች፣ ሰብዓዊ ቀውሶች እና የዓለም አቀፍ ሕግ መሸርሸር ላይ ጥልቅ ስጋታቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ለቀውሶቹ መፍትሔ ለመስጠት ፖለቲካዊ እና የውይይት መፍትሔዎች ቅድሚያ ሊሰጣቸው እንደሚገባ አሳስበዋል።

በሱዳን፣ በደቡብ ሱዳን፣ በሶማሊያ፣ በሊቢያ፣ በታላላቅ ሐይቆች ቀጣና፣ በሳህል እና በመላው አፍሪካ የሚካሄዱ አፍሪካ-መር የሰላም ሂደቶችን ለመደገፍ ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠዋል።

የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስባሪ ኃይልም ለሥራው በቂ ፋይናንስ የሚያገኝበት መንገድ ሊመቻች እንደሚገባ በውይይታቸው አንስተዋል።

በዲጂታል ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ፣ በአየር ንብረት እርምጃ እና ሁሉን አቀፍ ልማት በተለይም በአፍሪካ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ስትራቴጂ እና በሁለተኛው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ውጤቶች ላይ ትብብርን ማጎልበት እንደሚገባም ገልጸዋል።

አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ትብብርን ለማጠናከር የተስማሙት መሪዎቹ፣ 10ኛው ዓመታዊ የጋራ ኮንፈንስ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ተስማምተዋል።

በለሚ ታደሰ