Search

ለድርድር የማይቀርበው የሀገር ብሔራዊ ጥቅም

ሓሙስ ኅዳር 04, 2018 159

የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ግብ፤ ሀገሪቱን ከነሙሉ ፍላጎቷ እና ጥቅሟ ጉዞዋን ማስቀጠል ነው ሲሉ ምሁራን ገለጹ።

የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር የሆኑት ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ ማለት ነገ የት እንደርሳለን ብሎ በማሰብ ለመጻኢ ጉዞ መዘጋጀት እና ደህንነትን ማስጠበቅ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅምን የማስከበር ሂደት ውስጥ የውጭ እና የውስጥ ጫናዎች እንዳሉም አንስተው፤ ሕዝብ እና መንግሥት በመናበብ ለሀገራዊ ጥቅም ዘብ መቆም እንዳለባቸውም ነው የጠቆሙት።

ብሔራዊ ጥቅም ከዘመን ዘመን የሚቀያየር በመሆኑ፤ የአሁኑ ትውልድ የራሱ የሆነ የብሔራዊ ጥቅም ጥያቄ እንዳለውም ነው የገለጹት።

ኢትዮጵያ እና የባሕር በር ለዘመናት የተራራቁ አልነበሩም ያሉት ፕሮፌሰሩ፥ በታሪክ እጥፋት ምክንያት የባሕር በር ማጣቷን አስታውሰው፤ ኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት የነበራትን የማስመለስ ጉዳይ እንደሆነም አያይዘዋል። በዚህ ሂደት ውስጥ የኢትዮጵያ ፍላጎት ሰላማዊ መንገድ ብቻ እንደሆነም ገልጸዋል።

የሥራ አመራር አማካሪ እና ተመራማሪ የሆኑት ጌትዬ ትርፌ (/) በበኩላቸው፤ ከዚህ በፊት በነበሩ ወቅቶች የሀገሪቱ የብሔራዊ ጥቅም ፍላጎት ከሕዝቡ ጋር ወጥ ያለመሆን ክፍተት እንደተስተዋለበት አንስተዋል።

ብሔራዊ ጥቅምን በማዛባት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሂደት ጤነኛ እንዳይሆን የተለያዩ ጫናዎች እንደሚደረጉም ጠቁመው፤ አሁን ላይ በቁጭት እና በቁርጠኝነት ሕዝቡ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም ዘብ ሊቆም ይገባል ብለዋል።

በሜሮን ንብረት