Search

ከ70 ሺህ በላይ የዓለም ሰዎችን በአንድ ያሰባሰበው ጉባዔ

ሓሙስ ኅዳር 04, 2018 987

በቀጣይ 2027 ኢትዮጵያ እንድታዘጋጅ የተመረጠችበት የዓለም አየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በየዓመቱ 12-15 ቀናት ለሚሆን ጊዜ የሚካሄድ ነው።

ይህ የተባበሩት መንግሥታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባ ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መድረክ ከመሆን ባሻገር በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎችን ከመላው ዓለም የሚያሰባስብ ትልቅ ጉባኤ ነው።

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ተሳታፊዎችን በሚያሰባስበው በዚህ ጉባኤ የሀገራት ልዑካንን ጨምሮ ሲቪክ ማህበራት፣ ሚዲያዎች እንዲሁም የተለያዩ ድርጅቶችን በመወከል ታዳሚዎች ይሳተፋሉ።

እስካሁን በተደረጉ ጉባኤዎች ከፍተኛ ቁጥር ያለው ተሳታፊ የተገኘበት 2023 ተካሂዶ የነበረው ጉባኤ ነው።

በዚህ በተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ዱባይ ለአስራ ሁለት ቀናት ተካሂዶ በነበረው ጉባኤ 190 ሀገራት የተሰባሰቡ 70 ሺህ የሚበልጡ ተሳታፊዎች ተገኝተው ነበር።

ከዱባይ ቀጥሎ ከፍተኛ ህዝብ የተገኘበት ሌላኛው ጉባኤ ባሳለፍነው ዓመት በባኩ አዘርባጃን ተካሂዶ የነበረው የአየር ንብረት ጉባኤ ሲሆን በዚህም 56 ሺህ ሰዎች መሰባሰብ የቻሉበት ነበር።

በሦስተኛ ደረጃ ከፍተኛ ህዝብ እየተሳተፈበት የሚገኘው በብራዚሏ ቤለም እየተካሄደ የሚገኘው ጉባኤ ነው። በዚህ ጉባኤ ለመገኘት ከሀምሳ ሺህ በላይ ሰዎች ከመላው ዓለም መሰባሰብ ችለዋል።

ይህ እጅግ ከፍተኛ ሰዎችን የሚያሰባስብ ጉባኤ ለአየር ንብረት ለውጥ ከሚያደርገው አስተዋፅኦና ከዲፕሎማሲያዊ ጠቀሜያው ባሻገር አዘጋጅ ሀገራት ራሳቸውን የሚያስተዋውቁበትና ከቱሪዝም ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙበት ትልቅ መድረክ በመሆን ላይ ይገኛል።

ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎችን ከሚያሳትፈው ከዚህ ጉባኤ ልምድ በመነሳትም 2027 የሚካሄደውን የኮፕ32 ጉባኤ እንድታስተናግድ የተመረጠችው ኢትዮጵያ እስከ ሀምሳ ሺህ እንግዶችን ታስተናግዳለች ተብሎ ይጠበቃል።

በዋሲሁን ተስፋዬ