አንድ ሀገር ጤናማና ዘላቂ ዕድገት ማስመዝገብ የሚችለው በቁሳዊ መሠረተ ልማቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በሰው ተኮር የማኅበራዊ ልማት ሥራዎች ላይ ትኩረት ሲያደርግ መሆኑ ከበርካታ ሀገራት ተሞክሮ ማየት ይቻላል።
የማኅበራዊ ዘርፍ ግንባታ እንደ ሌሎች ግዙፍ መሠረተ ልማቶች ወዲያውኑ የሚታይና የሚጨበጥ ባይሆንም፣ ለሀገር ግንባታ ዘላቂና ወሳኝ መሠረት የሚጥል ዋልታ ነው።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ የታየው ተሞክሮም መንግሥት ለዜጎች ሁለንተናዊ ደኅንነት ቅድሚያ በመስጠትና የቆየውን የመደጋገፍ ባሕል በማላቅ እንዴት ወደ ተጨባጭ ሀገራዊ ስኬት መለወጥ እንደሚቻል ትልቅ ትምህርት የሰጠ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ አመራር ከመጡበት ጊዜ አንስቶ የማኅበራዊ ልማት እመርታን ለሀገር ግንባታ ለማዋል የጀመሯቸው ሥራዎች ዛሬ ኢትዮጵያን ብዙዎች ከሚገምቱት በላይ በጠንካራ መሠረት ላይ እየገነቧት ይገኛሉ።
ይህ ግዙፍ የማኅበራዊ ልማት ንቅናቄ መነሻው በ2010 ዓ.ም. ክረምት በአዋሬ ሰፈር በአንዲት አነስተኛ ጎጆ የተጀመረው የአቅመ ደካሞች ቤት ዕድሳት ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የራሳቸውን "የመደመር" መጽሐፍት ሽያጭ ገቢ ጭምር በመጠቀም የጀመሩት ይህ በጎ ተግባር፣ ዛሬ ወደ ግዙፍ ሀገራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተቀይሮ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ሕይወት እየለወጠ ይገኛል።
በዚህ ረገድ መንግሥት ደካማ እናቶችንና ቤተሰቦችን ከወደቁበት ለማንሳት ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር አሳይቷል። እስከ 2018 በጀት ዓመት አጋማሽ ድረስ ብቻ ከ329 ሺህ በላይ አዳዲስ ቤቶች ተገንብተውና ታድሰው ለአቅመ ደካማ ዜጎች ተላልፈዋል።
ይህም ዜጎች በገዛ ሀገራቸው በክብርና በደኅንነት እንዲኖሩ ከማስቻሉም ባሻገር፣ የማኅበራዊ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተከናወነ ግዙፍ ተግባር ነው።
ሌላው በማኅበራዊ ልማት ዘርፍ ታላቅ ስኬት የተመዘገበው "ትምህርት ለትውልድ" በሚል መሪ ቃል የተጀመረው የትምህርት ቤቶች ግንባታና ዕድሳት ንቅናቄ ነው።
ይህ ንቅናቄ ከመንግሥት በጀት ባለፈ የሕዝብንና የባለሀብቶችን አቅም በማስተባበር ከ140 ቢሊዮን ብር በላይ በማሰባሰብ ታሪካዊ ውጤት አስመዝግቧል። በዚህም 17 ሺህ 508 አዳዲስ ትምህርት ቤቶች የተገነቡ ሲሆን፣ 39 ሺህ 507 የሚሆኑት ደግሞ ሙሉ በሙሉ ታድሰዋል።
38 ሺህ 222 የቅድመ መደበኛ ትምህርት መማሪያ ክፍሎች እንዲስፋፉ ተደርጓል። ይህም ኢትዮጵያ የነገውን ትውልድ በዕውቀትና በክህሎት ለማነጽ የጀመረችውን ጉዞ የሚያፋጥን ፅኑ መሠረት ነው።
ከመሠረተ ልማት ግንባታው ጎን ለጎንም ዜጎች በኑሮ ውድነት እንዳይጎዱና ተማሪዎች በተሟላ ጤንነት ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የተጀመሩት የሥርዓተ ምግብ ፕሮግራሞች ተጠቃሽ ናቸው።
በትምህርት ቤት ምገባ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ብቻ ከ1.6 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች የመርሐ ግብሩ ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ9.5ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል። ይህም የተማሪዎችን የትምህርት አቀባበል ከማሻሻሉም ባለፈ፣ በአዲስ አበባ ብቻ በ8ኛ ክፍል የማለፍ ምጣኔ ላይ ባለፉት 5 ዓመታት የ40 በመቶ እድገት እንዲመዘገብ ምክንያት ሆኗል።
የዜጎችን ማኅበራዊ መረጋጋት ለማረጋገጥ መንግሥት የወሰደው የፊስካል እርምጃም የሚደነቅ ነው። የዓለም አቀፍ የነዳጅና የመሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ በዜጎች ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመቀነስ፣ መንግሥት በጠቅላላው 281 ቢሊዮን ብር የሚደርስ የነዳጅና የማኅበራዊ ድጎማ በማድረግ ለኢኮኖሚው መረጋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል።
የዚህ ማኅበራዊ ትስስር እና አብሮነት ጥንካሬ በይበልጥ የታየው ዓለምን ባስጨነቀው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት በተጀመረው የ"ማዕድ ማጋራት" መርሐ ግብር ነው።
ይህ እሴት እስከ 2018 የዘጠኝ ወራት አፈጻጸም ድረስ ቀጥሎ፣ 16.24 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች ማዕድ በማጋራት ማኅበራዊ ደኅንነትን ለመጠበቅ ተችሏል። በተጨማሪም በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ዘርፍ ከ2010 እስከ 2018 ባሉት ዓመታት ብቻ 157.3 ቢሊዮን ብር የሚገመት የኢኮኖሚ ዋጋ ያላቸው አገልግሎቶች ለኅብረተሰቡ ቀርበዋል።
ኢትዮጵያ በዘመሙ ጎጆዎች ዕድሳት የጀመረችው ይህ የማኅበራዊ ልማት ጉዞ፣ ዛሬ ወደ ሰፊ የትውልድ ግንባታ 63 ሚሊዮን ዜጎችን ወዳካተተ የጤና መድህን ተደራሽነት እና የኢኮኖሚ መረጋጋት ሥራዎች አድጓል። ባለፉት ዓመታት የተመዘገቡት እነዚህ ውጤቶች ሀገራችን ካጋጠሟት በርካታ ተግዳሮቶች በላይ በፍጥነት እየተገነባች መሆኗንና ዜጎችም በመረዳዳትና በአብሮነት የሚመጣውን ለውጥ በተግባር እያዩት መሆኑን ያረጋግጣሉ።
ይህ በራስ አቅም ላይ የተመሠረተና የሕዝብን ተሳትፎ ያረጋገጠ የማኅበራዊ ልማት ሞዴል ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና የምታደርገውን ጉዞ የሚያፋጥን ታላቅ ስኬት ነው።
ለሚ ታደሰ