በመካከለኛው ምሥራቅ እየተካሄደ ያለው ጦርነትና የሆርሙዝ ወሽመጥ መዘጋት በዓለም አቀፉ የነዳጅ አቅርቦት ላይ ከፍተኛ መስተጓጎል መፍጠሩን የጠቀሰው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፤ በዚህም ምክንያት በበርካታ ሀገራት የማደያዎች መዘጋትና ማኅበራዊ ቀውሶች እየተባባሱ እንደሚገኙ አመላክቷል።
ኢትዮጵያ ይህንን ከባድ ፈተና በተወሰነ ደረጃም ቢሆን መቋቋም የቻለችው መንግሥት ላለፉት ስምንት ዓመታት በውኃ፣ በነፋስ፣ በፀሐይ እና በጂኦተርማል የታዳሽ ኃይል ልማት ላይ ባከናወናቸው ግዙፍ ስትራቴጂያዊ ፕሮጀክቶች መሆኑንም አገልግሎቱ ገልጿል።
በተለይም የታላቁ ሕዳሴ ግድብን ጨምሮ የተለያዩ የኃይል አማራጮች እና የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ንቅናቄ ዛሬ የሀገራችንን የሕልውና ዋስትና መሆናቸውን ተጠቅሷል።
እነዚህ መሠረተ-ልማቶች አስቀድመው ባይዘጋጁ ኖሮ ኢትዮጵያ በከፋ የኢኮኖሚ መሽመድመድና የዋጋ ንረት ውስጥ ትወድቅ እንደነበር አመላክቷል። ከዚህ ባለፈም የጎዴ የተፈጥሮ ጋዝ ማጣሪያ የኢትዮጵያን የኢነርጂ ሉዓላዊነት ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑ ተጠቁሟል።
በአሁኑ ወቅት መንግሥት የዓለም አቀፍ የዋጋ ንረት ጫና በዜጎች ላይ እንዳይበረታ በማሰብ ለትልልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ ሊውል የነበረን በቢሊዮን የሚቆጠር በጀት ለነዳጅ ድጎማ እያዋለ እንደሚገኝ ያስታወቀው አገልግሎቱ፤ ይሁን እንጂ ይህ ድጎማ ለኮንትሮባንድና ለጥቁር ገበያ ዓላማ እንዲውል የማይፈቀድ መሆኑን አመላክቷል።
የነዳጅ ኮንትሮባንድን መከላከል የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን የማስከበር ጉዳይ በመሆኑ መንግሥት ከጸጥታ አካላትና ከኅብረተሰቡ ጋር በመሆን የማያዳግም እርምጃ መውሰዱን እንደሚቀጥልም ተገልጿል።
በአጠቃላይ የተጀመረው የኃይል ሉዓላዊነት ጉዞ ኢትዮጵያን ከአስከፊ አደጋ የታደገ በመሆኑ ኅብረተሰቡ ነዳጅን ከመቆጠብ ባለፈ ኮንትሮባንድን በመታገል የዜግነት ድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ያሳሰበው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት፤ የዛሬው መዋቅራዊ ሽግግር ለነገው ዘላቂ ብልጽግና መሠረት መሆኑን አመላክቷል።