በኢትዮጵያ የአንድ ቀን የናፍጣ አቅርቦት ከመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት በፊት ወደ ነበረበት 9 ሚሊዮን ሊትር እንዲመለስ መወሰኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ዛሬ በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
በመካከለኛው ምሥራቅ ግጭት ምክንያት የዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ መጨመር እና አቅርቦት ላይ መስተጓጎል መፈጠሩ ይታወቃል። ይህን ተከትሎም በኢትዮጵያ የአንድ ቀን የናፍጣ አቅርቦት ወደ 4.5 ሚሊዮን ሊትር ወርዶ ነበር።
አሁን የአንድ ቀን የናፍጣ አቅርቦት ወደ ቀደመው 9 ሚሊዮን ሊትር እንዲመለስ መወሰኑን ተከትሎ ከዛሬ ጀምሮ ከጅቡቲ ወደ አዲስ አበባ መጓጓዝ እንደሚጀመር የገለጹት የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ወደ ክልሎች ደግሞ ከነገ ጀምሮ መጓጓዝ ይጀምራል ብለዋል።
እስካሁን የቤንዚን እና የአውሮፕላን ነዳጅ ሙሉ በሙሉ ቀድሞ በነበረው መጠን እየቀረበ መሆኑንም የገንዘብ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የነዳጅ አቅርቦት መስተጓጎል ኢኮኖሚው ላይ የሚያደርሰውን ጫና ለመከላከል መንግሥት በልዩ ግዢ በከፍተኛ ዋጋ ነዳጅ ገዝቶ እያቀረበ መሆኑንም ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ አስረድተዋል።
በዚህም ምክንያት በአሁኑ ወቅት መንግሥት በየወሩ ቀድሞ ከነበረው በተጨማሪ 20 ቢሊዮን ብር እየደጎመ ነዳጅ እያቀረበ መሆኑን ነው የገለፁት።
በጌታቸው ባልቻ