Search

አሰብ፦ የተነጠቀው በር!

ማክሰኞ ሚያዝያ 20, 2018 68

የባሕር በር ለአንድ ሀገር የቅንጦት ጌጥ ሳይሆን፣ መተንፈሻ ሳንባ እና የሕልውናዋ ዋልታ ነው። ኢትዮጵያ በታሪኳ የባሕር ጌታ፣ የቀይ ባሕር አውራ የነበረች ቢሆንም፤ በተተበተበባት የቅኝ ግዛት ሴራ እና በታሪክ አጋጣሚ በተፈጸሙ የፖለቲካ ሸፍጦችና ስህተቶች ምክንያት ዛሬ ላይ የባሕር በር አልባ ለመሆን ተገዳለች። የአሰብ ጉዳይ፣ ከይገባኛል ጥያቄ ባሻገር በታሪክ፣ በሕግ እና በስትራቴጂካዊ ስሌት የተደገፈ የፍትሕ ጩኸት ነው።

ይህ የታሪክ ቁስል የሚጀምረው በ1862 ዓ.ም. ነው። ጣልያናዊው ጁሴፔ ሳፔቶ የሩባቲኖን የንግድ ኩባንያ በመወከል፣ 6 ሺህ ማሪያ ቴሬዛ ሰጥቶ አሰብን በግዥ ስም ጠቅልሎ ወሰደ። ይህ "የሽያጭ" ድርጊት፣ አሰብን ለመንጠቅ የተወጠነ የመጀመርያው የባዕዳን ሴራ ነበር።

ጣልያን እግሯን አሰብ ላይ ካጸናች በኋላ፣ የቅኝ ግዛት ጥማቷን ለማርካት ከ1892 እስከ 1900 ዓ.ም. ድረስ የድንበር ውሎችን በማዕከላዊ መንግስቱ ላይ ጫነች። ሆኖም እነዚህ ውሎች በዓለም አቀፍ የውል ስምምነት ሕግ (Vienna Convention) መሠረት ተቀባይነት የሌላቸው ነበሩ። ምክንያቱም የተፈረሙት በተፅዕኖ ወይም ጣልያን በፈጠረችው ወታደራዊ ጫና እና ማስፈራሪያ ስር በመሆኑ ነው። ይባስ ብሎ፣ በ1928 ዓ.ም. ፋሺስት ጣልያን ሉዓላዊቷን ኢትዮጵያን ስትወር፣ ቀደም ሲል የፈረመቻቸውን ውሎች በሙሉ በራሷ እጅ አፍርሳቸዋለች። በመሬት ላይ በምሰሶ እንኳን ባልተከለሉ እና ፈራሚዋ ራሷ ባፈረሰቻቸው ውሎች፣ የኢትዮጵያን የባሕር በር መብት ማሳጣት የሕግም ሆነ የታሪክ አመክንዮ የለውም።

የኢትዮጵያ የተፈጥሮ የባሕር በር መብት በዓለም አቀፍ መድረክ እውቅና የተነፈገበት ጊዜ አልነበረም። በ1921 ዓ.ም. በኢትዮጵያና በጣልያን መካከል የተፈረመው የሰላምና የንግድ ውል ኢትዮጵያ በአሰብ ወደብ በነፃነት እንድትጠቀም መብት ሰጥቷት እንደነበር አይዘነጋም። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቃት በኋላም፣ በ1943/44 ዓ.ም. የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ (ውሳኔ 390(V)) ኤርትራን ከአሰብ ጋር አጠቃልሎ ከኢትዮጵያ ጋር በፌዴሬሽን እንድትቀላቀል ሲወስን፣ የኢትዮጵያን ወደ ባሕር የመድረስ ታሪካዊ መብት በሚገባ አረጋግጦ ነበር።

ወደ ቅርቡ ታሪካችን ስንመጣ ደግሞ፣ የደርግ መንግሥት ለአሰብ ወደብ የነበረው ስትራቴጂካዊ ንቃት የሚደነቅ ነው። ደርግ በነበረው የተራዘመ ጦርነት እነዚህ ኃይሎች በአሰብ ላይ ሊፈጥሩ የሚችሉትን አደጋ አስቀድሞ በመረዳት፣ በ1972 ዓ.ም. ባወጣው አዋጅ አሰብን ከኤርትራ አስተዳደር ነጠላት። ይህ ስትራቴጂካዊ እርምጃ ይበልጥ ተጠናክሮ፣ በ1980 ዓ.ም. ሕገ-መንግሥት አሰብ በቀጥታ ለአዲስ አበባ ተጠሪ የሆነች "የአሰብ ራስ-ገዝ ክልል" ተብላ እንድትደራጅ አደረገ። ይህ አርቆ አሳቢነት፣ ወደፊት የቱንም ያህል ድርድር ቢመጣ እንኳን፣ አሰብ የኢትዮጵያ የህልውና አካል ሆና እንድትቀጥል የታለመ ስልታዊ እርምጃ ነበር።

ነገር ግን፣ ይህ ሁሉ የታሪክ፣ የሕግ እና የስትራቴጂ ጥረት በ1983 ዓ.ም. በተፈጠረው የፖለቲካ ሽግግር እንደ ሻማ ቀለጠ። የሀገርን ሉዓላዊ ግዛት አሳልፎ የመስጠት ሕገ-መንግሥታዊ ሥልጣን ያልነበረው የሽግግሩ መንግሥት፣ አሰብን በገዛ ፈቃዱ ለኤርትራ አሳልፎ ሰጠ። ለዚህ ውሳኔ የሚሆን አንድም ዓይነት ሕጋዊነት፣ መነሻ፣ አሠራር፣ የካቢኔ ወይም የምክር ቤት ውሳኔ አልነበረም። ይህ ታሪካዊ ስህተት በ1985 ዓ.ም. በተደረገው እና የኢትዮጵያን የባሕር በር መብት ፈጽሞ ከግምት ባላስገባው ሪፈረንደም ታትሞ ቀረ። የሕግና የታሪክ እውነት እንደገና የመገለጥ ዕድል አግኝቶ የነበረው በ1993ቱ የአልጄርስ ስምምነት ላይ ቢሆንም፣ የድንበር ኮሚሽኑ በፍትሕና ርትዕ (Ex Aequo et Bono) ላይ ተመስርቶ እንዳይወስን ሥልጣኑ በመገደቡ፣ አሰብን ለኢትዮጵያ የሚሰጡ የጂኦ-ፖለቲካና የታሪክ ማስረጃዎች ሳይደመጡ ታፍነዋል።

እውነተኝነትና ሀቅ እንደሚመሰክሩት፣ አሰብ በታሪክም ሆነ በተፈጥሮ ሕግ የኢትዮጵያ እንጂ የማንም አይደለችም። የተነጠቅነው በአታላይ ባዕዳንና በውስጥ ባንዳዎች ቅንጅት፣ በቅኝ ግዛት ኃያላን ወታደራዊ ጫና፣ እና በፖለቲካዊ ሸፍጥ በተሞሉ የቅርብ ጊዜ የፖለቲካ ውሳኔዎች ነው። ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት የባሕር በርን ጉዳይ ዳግም በብሔራዊ አጀንዳነት ማንሳቱ፣ ያለፈውን የታሪክ ስብራት ለመጠገን እና ሕጋዊ መብታችንን በሰላማዊ መንገድ ለማስመለስ የተጀመረ የፍትሕ ጥሪ ነው። አሰብ የተነጠቀው የሕልውናችን በር ነው፤ በሩ እስኪከፈት ደግሞ የኢትዮጵያ ትንፋሽ ምሉዕ ሊሆን አይችልም።

በአዶኒያስ ወ/አረጋይ