በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሠ ጫፎ የሚመራው የተጓደሉ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነሮች አስመራጭ ኮሚቴ ሥራውን በይፋ ጀምሯል፡፡
ከተለያዩ ተቋማት የተወከሉ ሰባት አባላት የተካተቱበት ኮሚቴው በፈቃዳቸው የለቀቁ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽነሮችን የሚተኩ እጩዎችን የማስመረጥ ሥራ እንደሚያከናውን ተገልጿል።
አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ጫፎ ኮሚቴው ሥራውን በጀመረበት ወቅት እንደገለፁት፤ አስመራጭ ኮሚቴው በሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የተጓደሉ 3 ኮሚሽነሮችን እንደሚያስመርጥ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ምክትል ኮሚሽነር፣ የሴቶች እና ሕፃናት ጉዳዮች ኮሚሽነር እንዲሁም የአካል ጉዳተኞች እና የአረጋውያን ኮሚሽነሮችን የማስመረጥ ሥራው ግልጽነትና ተጠያቂነት በተሞላበት መልኩ በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ እንዲጠናቀቅ በትኩረት ሊሠራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በፈቃዳቸው የለቀቁ ኮሚሽነሮችን ለማሟላት ጥቆማ የተጀመረ በመሆኑ ለሕዝብ ተደራሽ በማድረግ መስፈርቱን የሚያሟሉ ግለሰቦችን በተለያዩ አማራጮች ጥቆማ በመስጠት ማህበረሰቡ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ ቀርቧል፡፡