አራተኛው የቻይና የኑክሌር ኃይል የልማት ኮንፈረንስ እና የሼንዘን ዓለም አቀፍ የኑክሌር ኃይል ኤክስፖ በሼንዘን ኮንቬንሽን እና ኤግዚቢሽን ማዕከል እየተካሄደ ይገኛል።
የቻይና ግዙፍ ኩባንያዎችም በኤክስፖው ላይ እየተሳተፉ ነው።
በ"ዲጂታል ኢንተለጀንስ እና ፈጠራ የሚመራ ከፍተኛ ጥራት ያለው የኑክሌር ልማት" በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ያለው ኤግዚቢሽኑ፣ ሰው ሠራሽ አስተውሎት እና የኑክሌር ኢነርጂ እንዴት ሊጣመሩ እንደሚችሉ የማሳየት ዓላማ አለው፡፡
የታዳሽ ኃይል ኢነርጂ ሽግግርን እውን ለማድረግ እና የካርቦን ልቀት ቅነሳ ግቦችን ለማሳካት ሼንዘን የአረንጓዴ ኢነርጂ የወደፊት ዕጣ ፈንታ ማስጀመሪያ እንደሆነች ተገልጿል።
ኤክስፖው ላይ አዳዲስ እና ጥራት ያላቸው ምርቶች ለዕይታ የቀረቡ ሲሆን፣ ኑክሌርን በሰው ሠራሽ አስተውሎት በመምራት ታዳሽ እና ቀጣይነት ያለውን ኃይል ማግኘት የሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ግንዛቤ እንደሚፈጠር ሲጂቲኤን ዘግቧል፡፡
ቻይና እ.አ.አ. እስከ 2035 የሚተገበር የካርቦን ልቀትን በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ የሚያስችል ሀገራዊ ቃል ኪዳን (NDCs) ይፋ አድርጋለች። ይህንን ዓላማዋን ለማሳካትም የሰው ሰራሽ አስተውሎት እና የኑክሌር ኃይል ሞዴልን (AI + Nuclear Energy Model) ለመጠቀም እየሰራች ነው።
በለሚ ታደሰ