Search

ጁገል ግንብን የታደገው የኮሪደር ልማት

ሓሙስ ኅዳር 04, 2018 162

ጥንታዊቷ ሐረር በኮሪደር ልማቱ ይበልጥ ተውባለች። ከውበትም ባለፈ ልማቱ ቅርሶችን ለመጠበቅ ወሳኝ ሚና መጫወቱም ተገልጿል።
በሐረር ከተማ የተካሄደው የኮሪደር ልማት የጁገል ግንብን የታደገ መሆኑን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የሐረሪ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙክታር ሳሊህ ለኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ተናግረዋል።
ከተማዋ ምንም እንኳን ጥንታዊ ብትሆንም ያሏትን ታሪካዊ ፀጋዎች አጉልቶ ለማሳየት የሚረዱ የእድሳት ሥራዎች ባለመከናወናቸው ከተማዋ ውበቷ እንዳይጎላ አድርጎ መቆየቱንም አንስተዋል።
 
አሁን ላይ የኮሪደር ልማት ሥራው የተጎሳቆሉ አካባቢዎችን ቀይሯል፣ የተሽከርካሪ፣ የእግረኛና የብስክሌት መንገዶች፣ የመንገድ ዳር መብራትና ሌሎችም መሰረተ ልማቶች በስፋት በመገንባታቸው የከተማዋ የቀድሞ ገፅታ ተቀይሯል ይላሉ።
በጁገል ግንብ ዙሪያም አላስፈላጊ ግንባታዎች እና ሰፈራዎች ተበራክተው ታሪካዊ ቅርሱን ለአደጋ አጋልጠውት መቆየታቸውን አስታውሰው፤ የኮሪደር ልማት መጀመሩን ተከትሎ በቅርሱ ላይ ተደቅኖ የነበረውን አደጋ ማስወገድ እንደተቻለ ጠቅሰዋል፡፡
የኮሪደር ልማቱ ጁገል ግንብ ሕያውነቱ እንዲቀጥልና ታሪኩ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ መልካም አጋጣሚን ፈጥሯል ብለዋል፡፡
ሐረር በኮሪደር ልማቱ በእጅጉ ከተጠቀሙ ከተሞች መካከል ቀዳሚዋ ናት ሲሉም አቶ ሙክታር ገልፀዋል፡፡
ከተማዋ ጥንታዊና የቱሪስቶች መዳረሻ እንደመሆኗ የኮሪደር ልማቱ ተጨማሪ ድምቀትና ውበትን ከማጎናፀፉም በላይ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች ቁጥርም ሆነ ቆይታቸውን እንዲጨምር ማድረጉን አስረድተዋል።
በልማቱ ለከተማዋ ነዋሪዎች የሥራ እድሎች ተፈጥረዋል፣ ከተማዋ ምቹና ውብ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ የንግድ ተቋማት አምሽተው በመሥራትም ገቢያቸውን እያሳደጉ ነው ሲሉ አቶ ሙክታር ተናግረዋል።
የጁገል ግንብ አምስት ታሪካዊ በሮች ያሉት ሲሆን፤ ሐረርም በዩኔስኮ ከተመዘገቡ ታሪካዊ ከተሞች አንዷናት።
በአየነው አዲስ