የአፍሪካ ሕብረት በአውሮፓውያኑ 2007 የአህጉሪቱን የተራቆተ መልክዓ ምድር አረንጓዴ በማልበስ በተራቆቱ አካባቢዎች የሚኖሩ ሚሊዮኖችን ሕይወት የመለወጥ ዓላማ ያለውን የአረንጓዴ ግድግዳ ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል።
በፕላኔታችን ላይ ካሉት የሥነ-ህይወት ፕሮጀክቶች ሁሉ ትልቁ እንደሆነ የተነገረለት እና በአፍሪካ ውስጥ 8 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የአፍሪካ አረንጓዴ ግድግዳ ዘላቂነት እና ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስፈን ታልሞ የተጀመረ ነው።

ይህ ፕሮጀክት በ22 የአፍሪካ ሀገራት እየተተገበረ ሲሆን፣ በአህጉሪቱ የሚገኙ በሺህዎች የሚቆጠሩ የማኅበረሰብ ክፍሎችን እያንቀሳቀሰ ይገኛል።
ይህን ፕሮጀክት ለመደገፍ ከ14 ቢሊየን ዶላር በላይ መሰባሰቡም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በረሃማነትን የመዋጋት ኮንቬንሽን (United Nations Convention to Combat Desertification) ገጽ ላይ ተመላክቷል።
ዓለማውም በአውሮፓውያኑ 2030 አሁን በረሃማነት የሆነውን 100 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ወደ አረንጓዴነት በመመለስ 250 ሚሊዮን ቶን ካርቦን ማመንጨት እና 10 ሚሊዮን አረንጓዴ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር ነው፡፡
ስለተፈጥሮ እና ስለምድራችን ፈተናዎች የሚዘግበው ሞንጋቤይ (Mongabay) የተባለ ድረገጽ ባወጣው መረጃ ታላቁ የአፍሪካ አረንጓዴ ግንብ ፕሮጀክት ተስፋ የሚጣልበት ውጤት እያሳየ ነው፡፡
ድረ-ገጹ ያናገራቸው የዘርፉ ባለሙያዎች ፕሮጀክቱ እንዲሳካ ማኅበረሰቡ ጉዳዩን ዛፍ የመትከል ብቻ ሳይሆን አካባቢውን የሚለውጥ እንዲሁም የገቢ ምንጭ እንደሆነ አድርጎ እንዲመለከተው ግንዛቤ በመፍጠር ሁለንተናዊ ተሳትፎን እውን ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይገልጻሉ፡፡
በዚህ መንገድ ተሞክሮም በማሊ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ኒጀር፣ ጋና እና በሌሎች ከሰሀራ በታች ባሉ ሀገራት ውጤታማ እንደሆነ ባለሙያዎቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ታላቅ ራዕይን ሰንቆ የተነሳው የአረንጓዴ አሻራ
ዓለምን እያስጨነቀ ያለውን የአየር ንብረት ለውጥ አደገኛነት የተረዳችው ኢትዮጵያ በ2011 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ጀምራለች፡፡
የአረንጓዴ አሻራ የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ ፀጋዎች በመጠበቅ ምርት እና ምርታማነትን የሚያጎለብት እንዲሁም እድገቷን እና ብልፅግናዋን ለመጪዎቹ ትውልድ የሚያስቀጥል ነው፡፡
አረንጓዴ ኢኮኖሚ በመገንባት የኢትዮጵያን ብልፅግናን እውን የምታደርግበት ተግባርም ነው። የኢትዮጵያ የራሷ ልምላሜ ብቻውን በቂ ስላልሆነም አረንጓዴ አሻራን በጎረቤት ሀገራት እና በመላው አፍሪካ እንዲስፋፋም ብርቱ ጥረት እያደረገች ትገኛለች፡፡

ባለፉት ሰባት ዓመታት ዓመታት በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ከተተከሉት 48 ቢሊዮን ችግኞች ውስጥ ከ90 በመቶ በላይ መጽደቃቸው ተገልጿል፡፡
እንደ ግብርና ሚኒስቴር አረንጓዴ አሻራ ከተጀመረበት ወቅት አንስቶ በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የለም አፈር መከላትን ከ1.9 ቢሊየን ወደ 208 ሚሊየን ቶን ዝቅ እንዲል አስችሏል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአካባቢ ጥበቃ ኮንቬንሽን መስፈርት መሰረትም በ2011 ዓ.ም 17.2 በመቶ የነበረው የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ባለፉት ዓመታት በተሠራው የአረንጓዴ አሻራ ሥራ በአሁኑ ጊዜ 23.6 በመቶ በላይ ደርሷል፡፡
ኢትዮጵያ ደኗን ከዛሬ 40 ዓመት በፊት ወደ ነበረው 40 በመቶ ለመመለስ ስትራቴጂ ቀርጻ እየተንቀሳቀሰች ሲሆን፣ በ2030 አሁን ያለውን ከ23.6 በመቶ በላይ የደን ሽፋን 30 በመቶ ለማድረስም ግብ ተይዟል፡፡
ከአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ጎን ለጎን የደን ምንጣሮን የመቀነስ ሥራም ስለተሠራ ዓመታዊ የደን ውድመት ከ92 ሺህ ሄክታር ወደ 27 ሺህ ሄክታር ቀንሷል፡፡
በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ እንደ ማንጎ፣ አቮካዶ እና አፕል ያሉ ተክሎች የምሥራች ፍሬያቸውን ሰጥተው ለምግብነት ደርሰዋል፡፡
ይህ መርሐ ግብር ኢትዮጵያውያን በየጓሯቸው ችግኞችን ተክለው የሚንከባከቡበትን ባህል የፈጠረ ሆኗል፡፡
የኢትዮጵያ አረንጓዴ መርሐ ግብር "በአረንጓዴ አሻራ ዘላቂ የደን ልማት አያያዝና አጠቃቀም" በሚል ዘርፍ የተመድ የምግብ እና እርሻ ድርጅት (FAO) ዓለም አቀፍ ዕውቅናን አግኝቷል።
ዓለም ኢትዮጵያን ለምን መረጣት
ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመታት በኋላ የሚካሄደውን የዓለም አየር ንብረት ጉባኤ (COP32) እንድታስተናግድ ተመርጣለች። ከ50 እስከ 70 ሺህ ታሳታፊዎች ይታደሙበታል ተብሎ የሚጠበቀውን ጉባኤ የምታስተናግድ ሀገር አጀንዳ የመቅረጽ፣ ሀገራዊ ተነሳሽነቷን የማሳየት፣ ዲፕሎማሲዋን የማላቅ እና ኢኮኖሚዋን የማነቃቃት ዕድል ታገኛለች፡፡
ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ ካመጣችው ለውጥ በተጨማሪ በታዳሽ ኃይል ልማት ላይ እየሠራችው ያለው ሥራ ዓለም እየተጨነቀበት ላለው የዓለም አየር ንብረት ለውጥ ፈተና ያላትን ዝግጁነት ማሳያ ነው፡፡ ይህ አጀንዳዋ አፍሪካዊ ከመሆን አልፎ ዓለም አቀፍ ዕውቅናን ያገኘ ጉዳይ ነው፡፡

የአፍሪካውያኑ መዲና አዲስ አበባ ለዝግጅቱ ከሚመጥኑ ጥቂት የዓለማችን ከተሞች አንዷ መሆን ችላለች። ይህም አዲስ አበባ እንደገና ራሷን ያደሰችበት ጥበብ ዓለምን አስደንቋል። ዝግጁነቷንም በአንድ ዓመት ብቻ ባደረገቻቸው አህጉራዊ እና ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን በማዘጋጀት አረጋግጣለች፡፡
ከ25 ሺህ በላይ ተሳታፊዎች የተገኙበት እና የአፍሪካ አጀንዳ የተቀረፀበት 2ኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤን በስኬት ማዘጋጀቷ ራሷን ያዘጋጀችበት መጠን ማሳያ ነው፡፡
በለሚ ታደሰ