ኢትዮጵያ ያነሳችው የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ በአጭር ጊዜ ምላሽ እንዲያገኝ የተጀመረው ሠላማዊ ትግል ተጠናክሮ ሊቀጠል እንደሚገባ የባሕርዳር ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ለሃገራችን ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጉዳይ የህልውና እና የሉዓላዊነት ጉዳይ ነው ሲሉ ለኢቲቪ አስተያየታቸውን የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የባሕር በር የነበራት ሃገር መሆኗን ያነሱት ነዋሪዎቹ፤ ነገር ግን ባለፉት 30 ዓመታት ግልፅ ባልሆነ መልኩ የባሕር በሩ ተዘግቶባት ኢኮኖሚያዊ እና ዘርፈ ብዙ ተግዳሮቶችን እየተጋፈጠች ትገኛለች ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት መንግሥትን ጨምሮ መላው ኢትዮጵያውያን ያለምንም ልዩነት ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት እንድትሆን ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ይህ ብሔራዊ ጥቅምን ለማስከበር የሚደረገው ሠላማዊ የትግል እንቅስቃሴ ተስፋን የሚያጭርና የትውልዱን መፃዒ እድል የሚወስን አንገብጋቢ ጉዳይ ነው ሲሉ አያይዘው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያውያን በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ያሳዩትን ብሔራዊ ጀግንነትና አንድነት በባሕር በር ባለቤትነት ላይም ሊደግሙት እንደሚገባ ገልጸዋል።

አሁን ላይ የባሕር በር ጉዳይ ወቅቱን የዋጀ፣ ፍትሃዊና የትውልዱ ጥያቄ ነው የሚሉት የባሕዳር ከተማ ነዋሪዎቹ፤ የባሕር በር ባለቤትነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ሠላማዊ ትግል የዜግነት ድርሻቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
መላው ኢትዮጵያውያንም ይህ የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ዳር እንዲደርስ ከመንግሥት ጎን በመቆም ድጋፋቸውን እንዲያሳዩ ጥሪ አቅርበዋል።
በተስፋሁን ደስታ