የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፍ የ2018 በጀት ዓመት የመጀመሪያው ሩብ ዓመት የዕቅድ አፈፃፀም ግምገማ የሴክተር ጉባዔ በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።
በጉባዔው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)፥ በሀገሪቱ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፉን ለማሳለጥ የለውጥ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑን ገልጸው፤ በኢትዮጵያ ግዙፍ የሆነችው ጣና ነሽ ቁጥር ፪ ጀልባ ከወራት በፊት ወደ ባሕር ዳር ከተማ ገብታ ሥራ መጀመሯን አውስተዋል።
በጀልባዋ ጉዞ ውስጥ የኢትዮጵያን አንድነት ያየንበት ነው ያሉት ሚኒስትሩ፥ በጀልባዋ ጉዞ ለተባበሩት ኢትዮጵያውያን እና ባለድርሻ አካላት ሁሉ ምስጋና አቅርበዋል።
አክለውም የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ዘርፉ በእያንዳንዱ የኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ የጀርባ አጥንት መሆኑን ገልፀዋል።
ባለፉት ዓመታት በተለያዩ ዘርፎች ለተመዘገቡ ለውጦች ዘርፉ የተጫወተው ሚና ከፍተኛ ስለመሆኑም ነው የተናገሩት።
የሀገሪቱን የብልፅግና ጉዞ እውን ለማድረግ በዘርፉ የተሻሉ ተግባራትን በማከናወን፤ የጀመርነውን ሥራ አጠናክረን እንቀጥላለን ሲሉም ነው ሚኒስትሩ የገለፁት።
በሳሙኤል ወርቅአየሁ