የትግራይ ክልልንና ሌሎች የቀሩ አካላትን በምክክር ሂደቱ ለማሳተፍ ከሚደረገው ጥረት ጎን ለጎን፤ ለሀገራዊ መድረኩ አጀንዳዎችን ይፋ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ገለጸ።
ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በምክክሩ ውጤታማነት ዙሪያ ውይይት እያካሄደ ነው።
በመድረኩ 80 በመቶ የሚሆኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች እስካሁን በምክክር ሂደቱ እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተጠቁሟል።
የአጀንዳ ቀረፃውን በማጠናቀቅ ምክክር የሚደረግባቸውን አጀንዳዎች ይፋ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ዋና ኮሚሽነሩ ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ ተናግረዋል።
የምክክር ጉባዔውን ለመጥራትም ቅድመ ዝግጅቶችን እያከናወነ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ኮሚሽኑ ዲያስፖራውን ጨምሮ ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍል በምክክር ሂደቱ ለማሳተፍ ከፍተኛ ጥረት ሲያደረግ መቆየቱንም ነው የተናገሩት።
ዋና ኮሚሽነሩ እስካሁን በሂደቱ ተግዳሮቶች መኖራቸውንም አንስተው ከነሱም መካከል በትግራይ ክልል ያሉ ወገኖችና የተለያዩ ባለድርሻ አካላት አለመካተታቸው፣ ቁጥራቸው ውስን የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች በራሳቸው ምክንያት ለመሳተፍ ፈቃደኛ አለመሆናቸው፣ ሲሳተፉ ቆይተው የታቀቡ እንዲሁም በትጥቅ ትግል ላይ ያሉ ኃይሎች አለመካተታቸው የሚጠቀሱ ናቸው።
አብዛኞቹ ችግሮችም ፖለቲካዊ በመሆናቸው ፖለቲካዊ መፍትሔ እንደሚያስፈልጋቸው የምክክር ኮሚሽኑ ያምናልም ብለዋል ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ።
የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ ሰለሞን አየለ በበኩላቸው፤ እንደ ሀገር ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን ሀሉንም ያካተተ ሀገራዊ ምክክር አስፈላጊነቱን የጋራ ምክር ቤቱ በፅኑ የሚያንበት ነው ብለዋል።
የጋራ ምክር ቤቱ በምክክር ሂደቱ እየተሳተፉ የሚገኙትን ብቻ ሳይሆን በሂደቱ ያልተሳተፉትንም ትኩረት በመስጠት በንቃት እንዲሳተፉ እንደሚፈልግም ገልፀዋል።
በይመር አደም