በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል 20ኛውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ለማክበር በመናበብ የተሠሩ ሥራዎች ውጤታማ እንደሆኑ ተመልክተናል ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ተናገሩ።
በአፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር የተመራ ልዑክ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚከበረውን 20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን ለማክበር እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን ገምግሟል።
በክልሉ እየተሠሩ ያሉ የኮሪደር ልማት፣ የስቴዲየም ግንባታ ሂደት፣ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የሆቴሎች ዝግጅት እንዲሁም እንግዶችን ለመቀበል እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን የክልሉ ንዑስ ኮሚቴ ለዐቢይ ኮሚቴው አቀርቦ ተገምግሟል።
የቀሩ ሥራዎችን በፍጥነት ማጠናቀቅ እንደሚገባ እና ሆቴሎች በጥሩ ሁኔታ እንግዶችን እንዲያስተናግዱ ክትትል እንዲደረግ አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር አሳስበዋል።
የተጀመሩ ሥራዎች በዓሉ እስከሚከበርበት ቀን ድረስ በሚገባ ተጠናቅቀው በዓሉ ኢትዮጵያን በሚመጥን መልኩ እንደሚከበር አፈ ጉባኤው ተናግረዋል።
በግምገማው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ዛህራ ሁሙድ፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይን ጨምሮ የቋሚ ኮሚቴ ጸሐፊዎችና የጽ/ቤቱ አመራሮች ተገኝተዋል።
በኃይማኖት ከበደ