በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ያሉ የኮሪደር ልማት ሥራዎች የገጠር-ከተማ ትስስርን በማፋጠን ዘላቂ ብልጽግናን እንደሚያረጋግጡ የኢፌዴሪ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ተስፋሁን ጎበዛይ ገለጹ።
ኢትዮጵያ እየገነባች ያለውን ብዝኃ ዘርፍ ኢኮኖሚ በተሳለጠ የመሠረተ ልማት ትስስር ለማጎልበት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አገልግሎቱ አስታውቋል።
በከተማ እና ገጠር መካከል ያለውን የአኗኗር ዘይቤ ለማቀራረብ የገጠር የኮሪደር ልማት ወደ ትግበራ መግባቱ ይታወሳል።
የገጠር ኮሪደር የአርሶ እና አርብቶ አደሩን ሕይወት በማዘመን ምርታማነቱን የሚጨምርና ጤናማ የአኗኗር ሥርዐትን እውን ለማድረግ የሚያስችል ነው። ይህም ለታለመው ሀገራዊ ብልጽግና ዓይነተኛ መሠረት ነው።
የኮሪደር ልማቱ በገጠር እና ከተማ መካከል ያለውን መስተጋብር የሚያሳልጥ የግብርና ምርቶች እና የኢንዱስትሪ ውጤቶችን እንቅስቃሴ የሚፋጥን በውጤቱም የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን የሚያደርግ እንደሆነ አቶ ተስፋሁን ገልጸዋል።
በሚኒስትር ዴኤታው የተመራው ሚዲያ ልዑክ በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሆሳዕና ከተማ የኮሪደር ልማትን በከንቲባ ሳሙኤል ሽጉጤ አማካኝነት ጎብኝቷል።
በኮሪደር ልማቱ ዘመናዊ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች፤ የተሽከርካሪ፣ የብስክሌት እና እግረኛ መንገዶች ግንባታዎች ያሉበት ደረጃ ተጎብኝቷል።
የተጀመሩት ሥራዎች የሆሳዕና ከተማን ተወዳዳሪነት ከፍ የሚያደርጉና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዋን ከማፋጠን ባሻገር ገጽታዋን እንደሚቀይሩ ተመላክቷል።
ሆሳዕናን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ከተሞች እና የገጠር አካባቢዎች እየተከናወኑ ያሉ የኮሪደር ልማት ሥራዎች መንግሥት እያካሄደ ያለው አካታች እና ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን የማረጋገጥ ስትራቴጂ መገለጫዎች እንደሆኑም አቶ ተስፋሁን አስገንዝበዋል።
መንግሥት ለዚህ ግልጽ እና በተግባር እየተተረጐመ ያለ ስትራቴጂ ማስቀመጡንም ገልጸዋል። የየአካባቢው አስተዳደር ጥራት ባለው አግባብ ፈጠራና ፍጥነት ጨምሮ ስትራቴጂውን በመተግበር ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑንም በንግግራቸው አመላክተዋል።
በየዓመቱ የሚከበረውን የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን የሚያስተናግደው የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የኮሪደር ልማት ሥራዎችን እያፋጠነ ይገኛል። የሆሳዕና ከተማ ወቅታዊ እንቅስቃሴም ለዚህ ማሳያ ነው።
መንግሥት አካታች እና ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ሥርዐት እየገነባ እንደሚገኝ የበዓሉ ታዳሚዎች የሚገነዘቡበት ሥራ በሆሳዕና እየተከናወነ እንደሚገኘም አቶ ተስፋሁን ገልጸዋል። የኮሪደር ልማት ሥራዎቹ በፍጥነት እና በጥራት እየተከናወኑ መሆናቸውንም በማሳያነት አመላክተዋል።
የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የጸደቀበት እና ኢትዮጵያውን አንድ የጋራ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት የቃል ኪዳን ሰነድ እውን ያደረጉበት ኅዳር 29 ቀን የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦቸች እና ሕዝቦች ቀን በሚል ስያሜ ለ20ኛ ጊዜ ዘንድሮ በማእከላዊ ኢትዮጵያ ይከበራል።
የክልሉ መንግሥት ከመላው ኢትዮጵያ እና ከተለያዩ አገራት የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል በቂ ዝግጅት ማድረጉም በጉብኝቱ ወቅት መገለጹን የአገልግሎቱ መረጃ ያመላክታል።
በዚህ ወቅት ከ60 በላይ ከተሞች እና የተለያዩ የገጠር አካባቢዎች እየተገበሩት የሚገኙት የኮሪደር ልማት የለውጡ መንግሥት እውን በሆነ ማግሥት ከቢሮ እስከ ጓሮ በሚል የተጀመረ እና በስኬት እየተፈጸመ ከቢሮ እስከ ሀገር ወደሚል ስትራቴጂ ያደገ ሐሳብ ነው።
አጠቃላይ ዕሳቤውም የዘመነ እና ተፈጥሮን ከሰው ልጅ ጋር ያስማማ የመኖሪያ አካባቢ መፍጠር መሆኑን ነው የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ያስታወቀው።