በብራዚል ቤሌም እየተካሄደ በሚገኘው የኮፕ 30 ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ ኮፕ 32ን እንድታዘጋጅ ድጋፍ ላደረጉ ሁሉም ሀገራት እና ተሳታፊ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።
ኢትዮጵያ በኮፕ 32 የአስተናጋጅነት ኃላፊነት ለመቀበል ያላትን ቁርጠኝነት እና ዝግጁነት አረጋግጣለች ያሉት ሚኒስትሯ፣ ጉባኤው የአፍሪካን በጎ ምኞት፣ ግልጽ እና የጋራ እርምጃዎችን የሚንፀባረቅበት ይሆናል ብለዋል።
ጉባኤው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት አደጋ ላይ የመፍትሔ ሐሳቦች የሚፈልቁበት ይሆናል ሲሉም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ሁሉም ድምፆች የሚሰሙበት እና የሚከበሩበት ሁሉን አቀፍ ሒደት በመተግበር፣ ጠንካራ እና ትርጉም ያለው ውጤት ታስገኛለች ያሉት ሚኒስትሯ፣ ኮፕ 32 የየሀገራቱን የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ሥራዎችን ለመገምገም እና ጥረቶችን ለማስተካከል ወሳኝ ምዕራፍ ይሆናል ብለዋል።
የሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ረገድ የዓለምን አካሄድ በእጅጉ የሚቀይሩ እንደሚሆኑ ጠቁመው፣ ኢትዮጵያም በብቃት እና በተሻለ ሁኔታ ኮፕ 32ን እንደምታስተናግድ አረጋግጠዋል።
ከሁሉም አጋር አካላት እና የጉባኤው ተሳታፊዎች ጋር በቅርበት በመሥራት ለዓለም የአየር ንብረት ለውጥ አስፈላጊውን ሁሉ እናደርጋለንም ብለዋል።
አፍሪካ ዝግጁ ናት፣ ኢትዮጵያ በኃላፊነት ስሜት እና በቁርጠኝነት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤውን ለማስተናገድ ዝግጁ ናት ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በጌትነት ተስፋማርያም
#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #COP30 #COP32 #Climatechange