Search

ኢትዮጵያ ኮፕ 32ን እንድታስተናግድ መመረጧ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ለወሰደቸው እርምጃ የተሰጠ እውቅና ነው - ኢጋድ

ቅዳሜ ኅዳር 06, 2018 200

ኢትዮጵያ 32ኛውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ጉባኤን እንድታስተናግድ መመረጧ ለአየር ንብረት ለውጥ እርምጃና አረንጓዴ ልማት ቁርጠኝነቷ እውቅና የሰጠ መሆኑን የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) ገለጸ።

የድርጅቱ ዋና ጸሀፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ኢትዮጵያ ኮፕ 32 እንድታዘጋጅ መመረጧን ተከትሎ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልእክታቸውም፤ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ጉባኤውን ለማዘጋጀት መመረጧ በአየር ንብረት እና ልማት ላይ ያላት መሪነት እያደገ መምጣቱን የሚያሳይ ነው ብለዋል።

የአካባቢ ስነ ምህዳርን ወደ ነበረበት የመመለስ፣ ዘላቂ እድገትና የማይበገር አቅም ለመገንባት ያላትን ጠንካራ ቁርጠኝነት የሚያመላክትና ለዚህም ስራዋ እውቅና የሰጠ መሆኑን አመልክተዋል።

አረንጓዴ ዐሻራ እና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማት ስራ ማሳያዎች እንደሆኑም ነው የተናገሩት።

ኮፕ 32 ለኢጋድ ቀጣና ወሳኝ መድረክ መሆኑን ገልጸው ተቋሙ ድርቅ፣ የአየር ንብረት ለውጥ የፈጠረው የዜጎች መፈናቀልና የውሃ እጥረትን ጨምሮ ሌሎች አንገብጋቢ አጀንዳዎች የበለጠ ትኩረት እንዲሰጣቸው እንደሚያደርግ አመልክተዋል።