Search

አፍሪካ ለዓለም የምትናገረው ታሪክ በኢትዮጵያ ተሠርቷል - ዎዴ ማያ

ቅዳሜ ኅዳር 06, 2018 228

ጋናዊው በርትሆልድ ኮቢ ዊንክለር አኮን ወይም በማኅበራዊ ሚዲያ ሥራዎቹ ዎዴ ማያ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አፍሪካ ያለ ምንም እርዳታ ተዓምራት መሥራት እንደምትችል ያረጋገጠችበት እንደሆነ ተናግሯል፡፡

"ኢትዮጵያውያን ያለ ምንም የውጭ እርዳታ እንዴት ትልቁን የአፍሪካ ግድብ ገነቡ?" በሚል ርዕስ ዘጋቢ ፊልም የሠራው ማያ፤ ግድቡ አፍሪካውያንን የሚያስተሳስር መሆኑን ጠቅሷል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ትልቁ የአፍሪካ ግድብ ብቻ ሳይሆን በያዘው ታሪክ የዓለም ትልቁ ፕሮጀክት እንደሆነ ይናገራል፡፡

ግድቡ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ብሎ የተውለበለበበት ፕሮጀክት እንደሆነ ጠቅሶ፣ አፍሪካውያን አቅማቸውን ቢያቀናጁ ተዓምር መሥራት እንደሚችሉ ምስክር እንደሆነ አውስቷል፡፡

ኢትዮጵያውያን ነጻነታቸውን ለመጠበቅ ዓድዋ ላይ ያሳዩትን ኅብረት በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይም መድገማቸውን ተናግሯል፡፡

ግድቡ የተገነባው በኢንጂነሮች እና ባለሥልጣናት አመራር ብቻ ሳይሆን በሚሊዮኖች በሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ቀጥተኛ አስተዋፅዖ፣ መስዋዕትነት እና አንድነት እንደሆነ የጠቀሰው ዎዴ ማያ፤ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ውስጥ ልዩ የሆነ ስኬት እንደሆነ ገልጿል።

በሀገር ውስጥ እና በመላው ዓለም ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ቀን እና ሌሊት ላባቸውን እስካፈሰሱት ሠራተኞች የሁሉም ኢትዮጵያዊ አስተዋጽኦ እንዳለበትም ይናገራል፡፡

የአፍሪካ ምስል በዓለም ዙሪያ የተዛባ እንደነበር ጠቅሶ፣ አሁን አፍሪካ ላይ የነበረውን የተዛባ ትርክት የሚቀይር ሥራ መሠራቱን አውስቷል።

"አፍሪካዊ ስለሆነኩ እና ኩራት ስለሚሰማኝ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ማድረግ አለብኝ" የሚለው ዎዴ ማያ፤ "ጋና እና ሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ኢትዮጵያን የነጻነታቸው ተምሳሌት አድርገው እነዚህን ቀለሞች እንደተጠቀሙባቸው ሁላችሁም ታውቃላችሁ" በማለት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻነት ተምሳሌት መሆኗን ጠቅሷል፡፡

"የዚህ ግድብ ታሪክ እያንዳንዱን የአፍሪካ ሀገር ማንቃት አለበት፤ ሁሉም አፍሪካዊ ያለውን በማዋጣት አፍሪካን ለመገንባት መነሳሳት አለበት፤ የምንችለውን በማበርከት አህጉራችንን በጋራ ለመገንባት መነሳት አለብን ብዬ አምናለሁ፤ ለዚህም ጊዜው አሁን ነው" ብሏል ዎዴ ማያ።

ይህ የእኛ መነሳሻ መሆን አለበት የሚለው ማያ፣ ትክክለኛው የአፍሪካ ነጻነት ይኸ ስለሆነ እያንዳንዱን አፍሪካዊ ይህን ስኬት ማክበር አለበት ሲል ጥሪ አቅርቧል።

አፍሪካ ለዓለም ልትናገረው የሚገባው የትንሣኤ ታሪኳ ይህ እንደሆነ ጠቅሶ፣ "ኢትዮጵያውያን በኅብረት ዳግማዊ ዓድዋን እውን አድርገው ስላሳዩ እኮራባቸዋለሁ" ብሏል።

ግድቡ ኢትዮጵያን ከማብራት አልፎ ኢትዮጵያ ከጎረቤቶቿ ጋር የምትጋራው እንደሆነ የጠቀሰው ማያ፣ ይህም ኢትዮጵያ አፍሪካን የማስተሳሰር አቅሟን ያሳየችበት እንደሆነ ተናግሯል።

በለሚ ታደሰ

#EBC #EBCdotstream #GERD #Africa #panafricanism