Search

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የኢንተርፕረነርሺፕ ሳምንት (GEW) በኹነቶች ብዛት አንደኛ ደረጃን ያዘች

እሑድ ኅዳር 07, 2018 224

ዓለም አቀፍ የኢንተርፕረነርሺፕ ኔትወርክ (GEN) በየጊዜው በሚያወጣው ደረጃ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፉ የኢንተርፕረነርሺፕ ሳምንት (GEW) አንደኛ ደረጃ መያዟን የኢትዮጵያ ኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ፡፡
ውጤቱ የተገኘው የኢትዮጵያ ኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት (EDI) ባስተባበራቸው እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተሳተፉባቸው 4 ሺህ 375 ኹነቶች አማካኝነት መሆኑን በኢትዮጵያ ኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት የኢንተርፕረነርሺፕ ሥነ-ምህዳር ግንባታ ዳይሬክተር አቶ ዱጋሳ ተሰማ ገልጸዋል።
በውድድሩ ላይ 200 ሀገራት መሳተፋቸውን የጠቀሱት አቶ ዱጋሳ፣ መድረኩ እያንዳንዱ ሀገር ቀዳሚ የሚያደርገውን ሥራ የሚያቀርብበት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ የሳምንቱን አንደኛ ደረጃን የተቆጣጠረችው ብራዚልን እና ጆርዳንን አስከትላ እንደሆነም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዚህ መድረክ ተሳትፋ ይህን ደረጃ ማግኘቷ ዘርፉን ለማበረታታት እየሠራችው ላለው ሥራ ዕውቅና የሚሰጥ መሆኑን ጠቅሰው፣ ደረጃዋን ጠብቃ ለመጨረሻው ቀን እንድትደርስ የሁሉም አካላት ጥረት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ ኢንተርፕረነርሺፕ ሥነ-ምህዳር ካርታ ላይ የሚገባትን ቦታ ማግኘቷ በዘርፉ ላይ የሚሠሩ ባለድርሻ አካላትን ትኩረት እና ድጋፍ የሚያስገኝላት እንደሆነም ነው አቶ ዱጋሳ የጠቀሱት፡፡
ውጤቱ በነገው ዕለት ለ13ኛ ጊዜ በሚከፈተው የኢትዮጵያ ኢንተርፕረነርሺፕ ሳምንት በይፋ እንደሚገለጽ አቶ ዱጋሳ ተናግረዋል፡፡
መድረኩ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ተደማጭነት ያላቸውን የንግድ መሪዎች እና የኢንተርፕረነርሺፕ ሥነ-ምህዳር ባለድርሻ አካላት የሚገኙበት እንደሆነ ተጠቁሟል።
የዚህ ዓመት የዓለም አቀፉ ኢንተርፕረነርሺፕ ሳምንት የሚከበረው "በጋራ እንገንባ" በሚል መሪ ሀሳብ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዱጋሳ፣ መድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ስም ጎልቶ መታየቱ ትልቅ ትርጉም እንዳለውም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባለፈው ዓመት በመድረኩ ተሳትፋ ከአፍሪካ ሁለተኛ ከዓለም ደግሞ ስምንተኛ ደረጃ መያዟን አስታውሰው፣ በፈረንጆቹ እስከ ኅዳር 30 በሚቀጥለው የዘንድሮ ውድድር አንደኛ ደረጃዋን ጠብቃ እንድትቀጥል በሀገር ውስጥ የሚካሄዱ ኹነቶች ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ ተናግረዋል፡፡
ጉዳዩ በበርካታ መገናኛ ብዙኃንም ትኩረት አግኝቶ ኢትዮጵያም የሚገባትን ደረጃ እንድታገኝ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ አቶ ዱጋሳ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
 
በለሚ ታደሰ