የኢትዮጵያ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ጽሕፈት ቤቱን ቀድሞ ከነበረበት በመለወጥ መሐል ከተማ ወደ ቀድሞው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ሕንፃ አዛውሯል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ።
በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ በሕንፃው ላይ አስደናቂ የግንባታ ለውጥ እና ዘመናዊ የመሥሪያ ሥፍራ ጥበብን በማሳየት ለሠራተኞች እጅግ ምቹ የሆነ ስፍራንም መፍጠር ችሏል ሲሉ ገልፀዋል።
ተቋሙ በአምስት ዓመታት ጊዜ ውስጥ አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ሕይወታችንን በፍጥነት በመቅረጽ ውስጥ ያለውን ስፍራ በሚያንፀባርቅ እና ሀገራችንም በዚህ ዓለም አቀፍ የቴክኖሎጂ ውድድር በንቁነት መሳተፏን በሚያረጋግጥ መንገድ ከፍታ ላይ ደርሷል ብለዋል።
ኢንስቲቲዩቱ በጤና፣ በግብርና፣ በአገልግሎት ዘርፍ እያደረገ ያለው የመሪነት አስተዋፅዖውን እየተወጣ ሲሆን፤ በክላውድ ኮምፒውቲንግ፣ ትላልቅ የመረጃ ቋቶች፣ የመረጃ ፍለጋ፣ ሮቦቲክስ እና ኢመርሲቭ ቴክኖሎጂዎች አቅሙን በማጎልበት ላይ መሆኑን አስታውቀዋል።
በቅርቡ የተጀመረው የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ስታርት አፕ ማዕከል ደግሞ ይኽንን ከባቢ የበለጠ ያጠናክረዋል ሲሉ ገልፀዋል።
ዜጎች ሀሳብ ብቻ ይዘው በመምጣት ፕሮቶታይፕ ለመፍጠር፣ ለማባዛት ብሎም ከግሉ ዘርፍ ኢንቬስተሮች ጋር እንዲገናኙ እድል ያመቻቻል ብለዋል። እስከ አሁን 200 ሀሳብ ፈጣሪዎች በዚህ እድል ተጠቅመዋል ሲሉም አስታውቀዋል።