"ለሕዝባችን ጥያቄ ተጨባጭ ምላሽ እየሰጠንባቸው ካሉት ሥራዎች አንዱ የሆነውን የሦስት አዳዲስ ሆስፒታሎች አጠቃላይ የግንባታ ሒደት ገምግመናል" ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለፁ።
ሆስፒታሎቹ ከነበሩት የጤና ተቋማት የተሻለ (የላቀ) አገልግሎት የሚሰጡ ሆነው እየተገነቡ ሲሆን፣ ግንባታቸውም በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በአቃቂ ቃሊቲ፣ በንፋስ ስልክ ላፍቶ እና በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞች እየተገነቡ የሚገኙት ሆስፒታሎቹ፤ ከዚህ ቀደም ሆስፒታል ባልነበረባቸው አካባቢዎች መገንባታቸው የሕክምና ፍትሐዊ ተደራሽነትን ከማስፋት በተጨማሪ ከመላው ኢትዮጵያ ለሚመጡ ታካሚዎች አገልግሎት የሚሰጡ ይሆናል ብለዋል።

ሆስፒታሎቹ በአጠቃላይ 1 ሺ 500 አልጋ የሚኖራቸው ሲሆን ፣ አሁን ላይ ግንባታቸው እየተጠናቀቀ በመሆኑ ቀጣዩ ትኩረታችን ዘመናዊ የሕክምና መሳሪያዎችን ማስገባት ነው ሲሉ አስረድተዋል።
አዳዲሶቹ ሆስፒታሎች ለሕዝባችን ጥያቄ ተጨባጭ ምላሽ ከመስጠት ባሻገር በሚሰጡት ዘመናዊ የሕክምና አገልግሎት የልህቀት ማዕከል ሆነው የሚያገለግሉ ሲሆን፣ ከተማችንን የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ተጨማሪ አቅም የሚፈጥሩ ይሆናል ብለዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ከአዲስ ሆስፒታሎች ግንባታ በተጨማሪ በሚኒሊክ፣ በራስ ደስታ እና በዘውዲቱ ሆስፒታሎች አዲስ ሆስፒታል የመገንባት ያህል የማስፋፊያ ሥራ አከናውነናል ሲሉም ገልፀዋል።
ከእነዚህም ውስጥ የዘውዲቱ ሆስፒታል ማስፋፊያ ተጠናቅቆ ሥራ መጀመሩ ይታወቃል።