Search

ኢትዮጵያ ከሁሉም የዓለም አቅጣጫዎች ጎብኚዎችን እያገኘች ነው ፦ የቱሪዝም ሚኒስቴር

ዓርብ ኅዳር 12, 2018 171

በኢትዮጵያ አዳዲስ የውጭ ጎብኚዎችን ለመሳብ የማስተዋወቅ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ሲሉ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ ለኢቢሲ ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ተናግረዋል፡፡
ካለፈው ዓመት ጀምሮ አዳዲስ ቱሪስቶች እንዲመጡ የማስተዋወቅ ሥራ በመከናወኑ ከዩናይትድ አረብ ኢሚሬትስ፣ ከሳውዲ አረቢያ፣ ከህንድና ከቻይና ጎብኝዎች መምጣት ጀምረዋል ብለዋል፡፡
በሩብ ዓመቱ ከ376 ሺህ በላይ የውጭ ቱሪስቶች ኢትዮጵያን ጎብኝተዋል ያሉት ሚኒስትሯ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱንም ገልፀዋል፡፡
የውጭ ጎብኚዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ36 ሺህ ብልጫ እንዳለውም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመሪዎችና በተቋማት ደረጃ የሚያደርጓቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ እያስተዋወቁ መሆኑ ደግሞ የውጭ ጎብኚዎች ይበልጥ እንዲጨምሩ ማገዙን አስረድተዋል።
ከቱሪዝም የተገኘው ገቢ መጨመሩ፤ ኢትዮጵያን በምድረ ቀደምትነት ለማስተዋወቅ ባለፈው ዓመት የተሰሩ ሥራዎች ውጤት ማስገኘት መጀመራቸው ማሳያ መሆኑን አንስተዋል፡፡
የውጭ ጎብኚዎችን ቁጥር ይበልጥ ለማሳደግም በተለያዩ ሀገራት በሚካሄዱ የኢንቨስትመንት ፎረሞች ላይ ኤምባሲዎች እንዲያስተዋውቁ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
አዲስ አበባ የአህጉርና የዓለም አቀፍ ተቋማት መቀመጫ በመሆኗ ያሏትን ዕድሎች በአግባቡ በመጠቀም አዲስ የቱሪዝም የገቢ ምንጭ ለመፍጠርም ጥረቶች መጀመራቸውን አመላክተዋል፡፡
 
በየተመኙሽ አያሌው