Search

የ"መደመር" እና የ"ማዳኒ" ወግ

ዓርብ ኅዳር 12, 2018 321

ማዳኒጽንሰ-ሀሳብ ፈጣሪ እና አቀንቃኝ የአሁኑ የማሌዢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዳቱክ ሴሪ አንዋር ኢብራሂም ናቸው። "ማዳኒ" ሥርወ ቃሉ ዓረብኛ ሆኖ የሰለጠነ፣ የዳበረ እና ተራማጅ ማኅበረሰብ ማለት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማዳኒን እሳቤ የሀገራቸውን አንድነት ለመጠበቅ የመንግሥታቸው ዋና የፍልስፍና እና የፖሊሲ አጀንዳ አድርገው እየተጠቀሙበት ነው።

አንዋር ኢብራሂም 1995 ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የገንዘብ ሚኒስትር በነበሩበት ወቅት ነበር "ማሌዥያ ማዳኒ" ወይም "የሰለጠነች ማሌዥያየሚለውን እሳቤ በይፋ ያስተዋወቁት።

እሳቤው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የማሌዥያ ሰብዓዊ ክብርን ያረጋገጠ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገትን እንድታስመዘግብ እንዲሁም ማኅበራዊ ፍትህ እና መልካም አስተዳደርን እንድታረጋግጥ የተጠቀሙበት ሥነ-ምግባራዊ ማዕቀፍን ያጣመረ የአመራር ስልት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ 2022 ምርጫ ከመድረሱ በፊት ስድስት ዋና መርሆዎች የያዘውን እና ለተሻለች ማሌዥያ ይጠቅማል ያሉትን ራዕያቸውን ያሰፈሩበትን መጽሐፍ አሳትመዋል።

2023 በተደረገው ምርጫ 10ኛው የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተመረጡ፡፡ ሥልጣኑን ከተረከቡ በኋላም "የማሌዢያ ማዳኒ" የተሰኘ የፖሊሲ ማዕቀፍ ይፋ አደረጉ፡፡ ለመንግሥት አስተዳደር እና ለቀጣይ ዋና ዋና የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችም የማዳኒ ኢኮኖሚ ማዕቀፍ ሥራ ላይ አዋሉ።

ማዳኒ ስድስት ዋና ዋና ምሰሶዎች (Six Core Pillars) አለው፡፡ ጽንሰ-ሐሳቡ በማላይ ቋንቋ ምህጻረ ቃል ዙሪያ የተዋቀረ ሲሆን፣ መንግሥት ሕዝብን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ፖሊሲዎችን፣ የአስተዳደር እና የማኅበረሰብ እሴቶችን ለመቅረጽ የሚጠቀምባቸውን ስድስት ዋና እሴቶችን ይወክላሉ።

ከስድስቱ ምሰሶዎች አንዱ "ዘላቂነት" የሚል ሲሆን፣ ዘላቂ፣ ጠንካራ እና በአካባቢ ጥበቃ ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚን ማሳካት ነው፡፡ "ብልፅግና" ሌላው የማዳኒ ምሰሶ ነው፡፡ ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ዕድገትን ማሳካት እና የሁሉንም ዜጎች አጠቃላይ ደኅንነት እና የኑሮ ደረጃ ማሻሻል ነው፡፡

"ፈጠራ" ከማዳኒ ምሰሶዎች መካከል ነው፡፡ ፈጠራን ማበረታታት፣ እንደ ሰው ሠራሽ አስተውሎት ያሉ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም እና ዕውቀት ላይ የተመሰረተ ኢኮኖሚን መገንባት ነው እሳቤው፡፡ "አክብሮት" ማዳኒን የሚያቆመው ሌላኛው ምሰሶ ነው፡፡ በሕዝቦች መካከል ያለውን መግባባት ማሳደግ፣ በተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች መካከል ያለውን መከባበር ማጎልበት እና የሰውነትን ክብር መጠበቅ ነው፡፡

"እምነት (መተማመን)" የማዳኒ ምሰሶ ነው፡፡ መልካም አስተዳደርን እና ግልጽነትን ማስፈን እንዲሁም ሌብነትን በማስወገድ የሕዝቡን አመኔታ መገንባት ነው፡፡ "ርኅራሄ" ሌላው ማዳኒን ሙሉ የሚያደርገው ምሰሶ ነው፡፡ እንክብካቤ፣ ማኅበራዊ ፍትህን እና የተገለሉና ተጋላጭ የማኅበረሰብ ከፍሎችን ፍላጎት ማሟላት ላይ አጽንኦት ይሰጣል፡፡

የማዳኒ የመጨረሻ ግቡ ማሌዥያን በእስያ ውስጥ ግንባር ቀደም የኢኮኖሚ ኃይል ማድረግ ነው። በዚህም መሰረት ሀገሪቱን 30 ታላላቅ የዓለም ኢኮኖሚዎች ደረጃ ላይ ማስቀመጥ፣ ማሌዥያ ከዓለምአቀፍ ተወዳዳሪነት መረጃ ኢንዴክስ ውስጥ ከምርጥ 12 መካከል ማስቀመጥ እና እንደ ዲጂታል ኢኮኖሚ እና አረንጓዴ ኢኮኖሚ ባሉ ዘርፎች ላይ ማተኮር ግቡን ለማሳካት የተቀረጸ 10 ዓመታት የዕድገት ፖሊሲ አለው።

ማኅበራዊ ፍትህን በማረጋገጥ እና ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ላይ አተኩሮ የሚሠራ ሲሆን፣ ለዚህም የከፋ ድህነትን ማጥፋት፣ ከጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ጋር ሲነፃፀር የሠራተኛውን የገቢን ድርሻ መጨመር እና እንደ የጤና ክብካቤ፣ ትምህርት እና ማኅበራዊ ሴፍቲኔት ያሉ የማኅበራዊ ጥበቃ አውታረ መረቦችን ማጠናከር ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የሚሠሩ ሥራዎች እንደሆኑ የተመላከተው።

የጠቅላይ ሚኒስትር አንዋር ኢብራሂም ማዳኒ ማሌዥያ ሁለገብ ዕድገት እንድታስመዘግብ አስችሏታል፡፡ 2024 በተሠራው ዳሰሳም የሀገሪቱ ኢንቨስትመንት 14.9 በመቶ ከፍ ብሏል። የማሌዥያ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ምርት (GDP) 2023 ከነበረበት 3.6 በመቶ 2024 ወደ 5.1 በመቶ አድጓል፡፡ ባስመዘገበችው ዕድገትም የበጀት ጉድለቷን መቅረፍ ችላለች፡፡ ሀገሪቱ 2024 ከነበረችበት 34 የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚ ደረጃ 11 ከፍ በማለት 2025 ወደ 23 ላይ ተቀምጣለች።  

መደመር

መደመር ከእሳቤ እስከ መንግሥት ያደገ ኢትዮጵያ እተየመራችበት ያለ ፍልስፍና ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) የአመራር ፍልስፍና የሆነ መደመር ተፈጥሮን ማዕከል አድርጎ ለኢትዮጵያ ችግሮች ሀገር በቀል መፍትሔዎችን ያመጣ ነው፡፡ የመደመር እሳቤ ኃይል በማስባሰብ መርህ ያምናል፡፡ አብሮ የማደግ እሴትም እንዲዳብርም ይሠራል፡፡ የመደመር ዋና ግቡ ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና ማማ ማውጣት ነው፡፡

የመደመር ምሰሶዎችም ሀገራዊ አንድነት፣ የዜጎች ክብር እና ብልፅግና ናቸው፡፡ መደመር ስለ "ሀገራዊ አንድነት" ሲያወሳ ማንነታችን እንዳንለያይ ሆኖ የተጋመደ፣ የተሰናሰለ እና የተወሐደ እንደሆነ ይጠቅሳል፡፡ ሀገራዊ አንድነት ምርጫ ብቻ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ እንደሆነም አጽንኦት ይሰጣል፡፡

"የዜጎች ክብር" ሌላኛው የመደመር ምሰሶ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ክብራቸው ተጠብቆ እና ሀገራቸውን መከታ አድርገው እንዲኖሩ መሥራት ነው፡፡ ግለሰባዊ ነጻነት እና ማኅበረሰባዊ ደኅንነትን ማቀንቀን የዚህ ምሰሶ ዋና ሀሳብ ነው፡፡

ሦስተኛው የመደመር ምሰሶ "ብልፅግና" ነው፡፡ ዜጎች ሥጋዊ፣ የስም እና የነጻነት ፍላጎቶችን በቀጣይነት ማሟላት እንዲችሉ አቅማቸውን ማሳደግ ነው፡፡ ይህ መሰረታዊ ፍላጎቶችን ከመሟላት ያለፈ መንፈሳዊ ብልፅግናን ያካትታል፡፡ መደመር ሰው ሰው በመሆኑ ብቻ ክብሩና ነጻነቱ እንዲከበር ዘብ መቆም ማለት ነው።

መደመር ሦስት የሥነ-ምግባር እሴቶችም አሉት፡፡ ከእነዚህ እሴቶች መካከልም ይቅር ባይነት፣ ፍቅር እና አቃፊነትን የሚያካትተው የሞራል እሴት አንዱ ነው፡፡ ሥነ ምግባራዊ ብልሽትን በማስወገድ፤ ከጠባብ የግል እና የቡድን ጥቅም ይልቅ የጋራ ጥቅሞችን ቅድሚያ መስጠትን ነው፡፡ ኃላፊነትን መውሰድ ሌላው የመደመር የሞራል እሴት ነው። ሕግን ማክበር መደመር በትከረት የሚሠራበት የሥነ-ምግባር እሴት ነው፡፡

ምንም ነገር ምሉዕ ስላልሆነ ትብብር እና ፉክክርን አመጣጥኖ በተአቅቦ ሚዛን መኖር የመደመር ብያኔ ነው፡፡ በመደመር ዕይታ መሠረት የሰው ልጅ የፉክክርም ሆነ የትብብር፣ የዘረኝነትም ሆነ የሰላማዊነት ዝንባሌው በእጁ ላይ እንደሆነ በመደመር ላይ ተጠቅሷል። የሰው ልጆች ኅብረት መሥርተው እርስ በርስ ተደጋግፈው በመኖር የሚታወቁ ፍጡራን በመሆናቸው የሚፈለገውን ዕድገት ለማምጣ መደመር ትክክለኛው መንግድ መሆኑነ ነው የሚያወሳው፡፡ ሌላው ብያኔው ደግሞ ወረትን ማካበት ነው፡፡ ወረትን ማካበት ትላነትን ሳያፈርሱ ከትላንት መልካሙ ወረት ዛሬ ላይ እየደመሩ መሄድ፣ ለነገ ደግሞ እሴትን ማኖር ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(/) የኢትዮጵያ ፖለቲካ ችግር ስብራት ዋነኛው ጉዳይ የጠላቶቿ አጀንዳ የሆነው መለያየት ነው ይላሉ፡፡ ውጤቱም በዘር፣ ሃይማኖት፣ ፆታ፣ ሰፈር፣ መንደር እየተባለ መለያየት እንደሆነ እና ለዚህ መፈወሻ መድኃኒቱ ደግሞ መደመር ብቻ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና ማማ ለማውጣት የተያዘውን ግብ ለማሳካትም አካታች አንድነትን በማምጣት፣ ተቋማትን በማጠናከር እና የፖለቲካ ነጻነትን በማምጣት ጠንካራ የዴሞክራሲ መሰረትን መጣል እንደሚገባ መደመር በግልጽ አስቀምጦታል፡፡

ሚዛናዊ ኢኮኖሚን በመገንባት፣ መዋቅራዊ ሽግግርን እውን በማድረግ እና የጋራ ብልጽግናን አረጋግጦ ሀገርን ወደተሟላ የኢኮኖሚ ዕድገት እና ብልጽግና ማሸጋገርም የመደመር እሳቤ ሌላው መንገድ ነው፡፡

የአፍሪካ ቀንድ ላይ ትብብርን ማጽናት፣ ገለልተኛ ዲፕሎማሲ እና የአፍሪካ መሪ መሆን የመደመር የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ግብ ነው፡፡

ኢትዮጵያ በመደመር እሳቤ ተመርታ ታላቅ እምርታ እያሳየች ትገኛለች፡፡ ከስንዴ ልመና ከመውጣት እስከ የባሕር በር አጀንዳ ድረስ ያሉት ውጤቶች በመደመር እሳቤ የመጡ ናቸው፡፡ ባለብዙ ዘርፍ የኢኮኖሚ ፖሊሲው ኢትዮጵያ ሀብቷን ለይታ እንድትጠቀም እያስቻላት ነው፡፡ ኢትዮጵያ በጽንፈኝነት እና በውጭ ተፅዕኖ መካከል ሆና መቀጠል ብቻ ሳይሆን አስደማሚ የኢኮኖሚ ዕድገት ያስመዘገበችው በመደመር እሳቤ ላይ የተመሰረት ችግርን የሚቋቋም (shock absorber) ስትራቴጂ በመከተሏ ነው፡፡

በዚም መሰረት ከስብራት ወደ ማንሰራራት መጥታ ባለፈው ዓመት ብቻ 9.1 በመቶ አጠቃላይ የኢኮኖሚ ዕድገትን አስመዝግባለች፡፡

በለሚ ታደሰ