በብራዚል ቤሌም ሲካሄድ የቆየው 30ኛው የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ እንዲጠናቀቅ ከተያዘለት አንድ ቀን ዘግይቶ የመዝጊያ ሥነ ሥርዓቱ ዛሬ ተካሂዷል።
ላለፉት ሁለት ሳምንታት የተካሄዱ ድርድሮች እና ስምምነቶችን ያፀደቀው ዐቢይ ጉባኤው ዛሬ የመዝጊያ ሥነ ሥርዓቱን አድርጓል።
በዚሁ ስብሰባ ላይም 32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ለማዘጋጀት በኢትዮጵያ የቀረበው እና በአፍሪካ ቡድን የተደገፈው ሃሳብ ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት አግኝቶ፣ ፀድቆ በይፋ ተበስሯል።
በ2027 ኮፕን የማዘጋጀት ተራ የአፍሪካ በመሆኑ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ጥያቄ አፍሪካውያን ወንድሞች ተስማምተው መደገፋቸው እና ወደ ዐቢይ ጉባኤው መተላለፉ ይታወሳል።
ዐቢይ ጉባኤውም ይህንኑ የኢትዮጵያ ጥያቄ ተቀብሎ ማፅደቁን ዛሬ በይፋ ገልጿል።
በዚህም ኢትዮጵያ 32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በፈረንጆቹ 2027 አሰናድታ እንግዶቿን ትቀበላለች።
አረንጓዴ ዐሻራን ጨምሮ ያለፉት ዓመታት የአየር ንብረት ለውጥ መከላከል ወሳኝ እርምጃዎች፣ በአዲስ አበባ የተካሄደውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ በስኬት ማስተናገዷ፣ በስመ ጥሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምክንያት የአየር ግንኙነት ሰፊ እድል መኖሩ እና ኢትዮጵያ በፖለቲካ ቁርጠኝነቷ ጭምር በተግባራዊ እርምጃዎች ግንባር ቀደም መሆኗ ጉባኤውን እንድታሰናዳ ካስመረጧት ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ ልዩ ጉባኤዎችን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶችን በብቃት ማስተናገዷ፣ ኮፕ 32 ወደ ኢትዮጵያ እንዲያመራ ማስቻሉ ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አፍሪካውያን ወንድሞች ለሰጡት ድጋፍ ምስጋና ማቅረባቸው ይታወሳል።
ኮፕን የማዘጋጀት እድል ትልቅ ትርጉም ያለው በመሆኑ ኢትዮጵያ ያሳየችውን አህጉራዊ መሪነት ወደ ዓለም ያሳድገዋል ተብሎ ይጠበቃል።
ጉባኤውም እንደ ፈረንጆቹ አቆጣጠር ከህዳር 8 እስከ 19፣ 2027 በአዲስ አበባ የሚካሄድ ይሆናል።
በሀብታሙ ተክለስላሴ