ሠርተው የማይደክሙ ክንደ ብርቱ፣ እንደንብ ታታሪ እና ጥበበኛ በመሆናቸው በመጦሪያ ዕድሜያቸው ለልጆቻቸው የሥራ ዕድል እየፈጠሩ ይገኛሉ።
እኒህ ለበርካቶች ተምሳሌት የሆኑት የ78 ዓመት አዛውንት በሰሜን ጎንደር ዞን ደባርቅ ከተማ የሚኖሩት አቶ እሸቴ አቸነፈ ናቸው።
እርጅና መጣሁ ሲላቸው አልሸነፍ ባይነትን ተላብሰው የንብ ማነብ ሥራን በማከናወን የማር ምርት ለገበያ ያቀርባሉ።
ዕድሜ ቁጥር ነው የሚሉት አቶ እሸቴ፥ ፈተናዎችን በጽናት በማለፍ ሥራን በወቅቱ በጥንካሬ እና በብልሃት መከወን በመቻላቸው ለስኬት መብቃታቸውን እና በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን ይገልጻሉ።
95 የንብ ቀፎዎችን በመጠቀም ማር እያመረቱ ለማኅበረሰቡ ንፁህ ማር ከማቅረባቸው ባሻገር ለ8 ልጆቻቸው የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።
ባለፈው ዓመት ከ200 ኪሎ ግራም በላይ የማር ምርት ማግኘታቸውን ጠቅሰው፤ ዘንድሮ ደግሞ ከ400 ኪሎ ግራም በላይ የማር ምርት ለማግኘት እየተጉ መሆናቸውን ለአሚኮ ተናግረዋል።
#ebcdotstream #diligence #beekeeping