Search

ለመሆኑ ዛሬ ስንት እርምጃ ተራመዱ?

ማክሰኞ ጥር 19, 2018 139

በቀን በአማካይ 10,000 እርምጃዎችን የመራመድ ልምድ ለጤናችን እጅግ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን እንደሚያስገኝ ያውቁ ኖሯል?

በአማካይ 10 ሺህ እርምጃዎችን አልያም ቢያንስ 8 ኪሎ ሜትር ገደማ የሚሆን ርቀትን በየእለቱ መጓዝ የልብን ጤንነት ለማሻሻል፣ የደም ዝውውርን ለማሳለጥ፣ የአእምሮ ውጥረትን ለመቀነስ እና እንደ ስኳርና የደም ግፊት ያሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል ትልቅ አቅም አለው።

አንድ የከተማ ሰው በቤት ውስጥ በሚያደርገው የዕለት ተለት እንቅስቃሴ በምግብ ዝግጅት፣ በጽዳት እና ሌሎችም በአማካይ 1,000 እስከ 3,000 እርምጃ ሊራመድ ይችላል። ይህም ለጤና ከሚያስፈልገው ግብ ለመድረስ ተጨማሪ የእግር ጉዞ አስፈላጊ መሆኑን ያሳያል።

ጤናማ የአኗኗር ዘይቤን ለመከተል ለወሰኑ ሰዎች ደግሞ በስማርት ስልኮች ላይ የሚጫኑ እንደ StepUp Strava እና Google Fit ያሉ መተግበሪያዎች ሁነኛ አማራጭ ተደርገው ቀርበዋል።

እነዚህ በኤአይ የተደገፉ በስልካችን ላይ የሚገኙ መተግበሪያዎች ለአንድሮይድ እና iOS ተጠቃሚዎች ምቹ ሆነው የቀረቡ ሲሆን፣ ከግል እንቅስቃሴ መቆጣጠሪያነት ባለፈ ማህበራዊ መስተጋብርን ከጤና ጋር በማስተሳሰር መቅረባቸው ልዩ ያደርጋቸዋል።

የመተግበሪያዎቹ ተጠቃሚዎች ከጓደኞቻቸውና ከቤተሰቦቻቸው ጋር በመገናኘት የእርምጃ ብዛታቸውን በፉክክር መልክ እንዲያሳድጉ ያበረታታሉ። ይህም ለብቻ ከመንቀሳቀስ ይልቅ ከሌሎች ሰዎች ጋር በመፎካከር የተሻለ ተነሳሽነትን ይፈጥራል።

በአሁኑ ወቅት እነዚህ ቴክኖሎጂዎች በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) የታገዙ በመሆናቸው፣ የእያንዳንዱን ሰው የእንቅስቃሴ ደረጃን በመተንተን ለሰውነታችን የሚስማማ ምክርና ማሳሰቢያ መስጠት የሚችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እነዚህን አፕሊኬሽኖች የዕለት ተለት ሕይወታቸው አካል አድርገዋቸዋል። በሀገራችን ኢትዮጵያም የስማርት ስልኮች ተጠቃሚ ቁጥር መጨመር ለጤና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ትልቅ እድል ከፍቷል።

የከተማ ህይወት እንቅስቃሴን የሚገድብና ለእንቅስቃሴ አልባ አኗኗር የሚያጋልጥ በመሆኑ፣ በስልካችን ወይም በስማርት ሰዓታችን የምናገኛቸው የጤና መተግበሪያዎች እንቅስቃሴያችንን እንድንቆጣጠር እና የነቃ አኗኗር ዘዬን እንድንከተል ይረዱናል።

ከስማርት ከስልኮች ጋር የተሳሰሩ ስማርት ሰዓቶችም እርምጃችንን፣ የልብ ምታችንንና የምናቃጥለውን የካሎሪ መጠን በትክክል ይመዘግባሉ። ይህ ዘመናዊ የጤና ክትትል ዘዴ ማህበረሰባችን የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለተሻለ የጤና ለውጥ እንዲጠቀም እና በንቃት በመንቀሳቀስ ጤናማ ትውልድ እንዲገነባ ትልቅ ፋይዳ አለው።

በዘመናዊው ዓለም ቴክኖሎጂ ጤናችንን በእጅ ስልካችን አለፍ ሲልም በስማርት ሰአታችን የምንከታተልበትን መንገድ በማመቻቸት አኗኗራችንን ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል ለማለት ይቻላል። በአሁኑ ወቅት ስማርት ስልኮች ለመገናኛ ብቻ ሳይሆን የጤናችን ጠባቂ በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።

ለእርምጃ፣ ለአካል ብቃት እንቅስቃሴ እና ለአጠቃላይ ጤና ተስማሚ የሆኑ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በቀላሉ የሚሰሩ አምስት አፕሊኬሽኖች እነሆ፦

🚶‍➡️Google Fit: በጣም ቀላሉና ከማንኛውም አንድሮይድ ስልክ ጋር በቀላሉ የሚተሳሰር ነው። "Heart Points" በሚል መለኪያ የልብዎን ጤንነት ለመጠበቅ ምን ያህል መንቀሳቀስ እንዳለብዎ ይመራዎታል።

🚶‍➡️StepUp (Pedometer): ከጓደኞች ጋር ተቀዳድሞ ለመራመድ ምርጡ አፕ ነው። በስልክዎ ያሉ ሰዎችን በመጋበዝ የእርምጃ ብዛትዎን በደረጃ ሰንጠረዥ (Leaderboard) ማየት ያስችላል።

🚶‍➡️Samsung Health: ሳምሰንግ ስልክ ለሚጠቀሙ ሰዎች እጅግ ዘመናዊ አማራጭ ሲሆን፣ ከእርምጃ በተጨማሪ የምግብ፣ የውሃ እና የእንቅልፍ ሁኔታን ለመመዝገብ ይረዳል።

🚶‍➡️Strava: ረጅም ርቀት ለሚራመዱ ወይም ለሚሮጡ ሰዎች የተመረጠ ነው። ካርታ ላይ የተጓዙበትን መስመር የሚያሳይና ለማህበራዊ ሚዲያ ተስማሚ የሆኑ ስታቲስቲኮችን የሚያዘጋጅ ነው።

🚶‍➡️Pacer Pedometer: ይህ አፕሊኬሽን ስልኩን ኪስዎ ውስጥ አስቀምጠው ቀኑን ሙሉ እርምጃዎን በዝምታ እንዲቆጥር ያደርጋል። የግል የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ቪዲዮዎችንም ያካትታል።

እነዚህን አፕሊኬሽኖች Play Store ወይም App Store በነፃ በማውረድ መጠቀም ይችላሉ።

ለመሆኑ ዛሬ ስንት እርምጃ ተራመዱ? ውጤትዎን በኮሜንት ያጋሩን!

#ጤና #StepUp #ኢቢሲ #Ethiopia #FitnessMotivation #SmartLiving