Search

ቆጮን ወደ ኬክ እና ኩኪስ ቀይሮ ለሠርግና ልደት እያቀረበ ያለው የምግብ ማቀነባበሪያ

ማክሰኞ ታኅሣሥ 14, 2018 306

ማህበሩ በአርባምንጭ ከተማ ሲቀላ ኢንዱስትሪ ክላስተር ማዕከል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፤ የተቋቋመው በ2015 ዓ.ም ነው።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት የተመራ የሚዲያ ባለሙያዎች እና የሥራ ኃላፊዎች ቡድን የድርጅቱን የሥራ እንቅስቃሴ ጎብኝቷል።

ወጣት የትምወርቅ ሰይፉ በድርጅቱ የፕሮዳክሽን ማናጀር ናት። እናቶች ቆጮ ፍቀው ለመብላት 3 እና 4 ወራት ይፈጅባቸው የነበረውን ማህበሩ በ1 ሳምንት ብቻ ማጠናቀቅ የሚያስችል የምግብ ማቀነባበሪያ ማሽን ድጋፍ ተደርጎለት ሥራ መጀመሩን ትገልፃለች።

ድርጅቱ በአሁኑ ወቅት የእናቶችን ድካም የሚያቃልሉ ማሽኖችን ከማቅረብ በተጨማሪ ቆጮን በኩኪስ፣ በኬክ፣ በቡላ ዱቄት እና በሌሎች የተቀነባበሩ ምርቶች ለገበያ በማቅረብ ተወዳጅነትን እያተረፈ መጥቷል ትላለች።

እናም በርካቶች ለሠርግ፣ ለልደት፣ ለቀለበት ፕሮግራም እና ለአኒቬርሰሪ የቆጮ ኬኮችን ምርጫቸው እያደረጉ ስለመሆኑ ትናገራለች።

ማህበሩ ከክልሉ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን እና ከአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር በ2015 ዓ.ም ሉሲ የእንሰት መፋቂያ፣ ማብላያና እንዲሁም ማቀነባበሪያ ወደ ሥራ ማስገባቱን ገልጻለች።

በዚህም በእንሰት ምርት ላይ እሴት በመጨመር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳጅ ምግብ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን ነው ወጣቷ የምትናገረው።

በክልሉ ለሚገኙ 40 ማህበራት ስልጠና በመስጠት እና ማቀነባበሪያ ማሽኑን ተደራሽ በማድረግ ከ200 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉ ተገልጿል።

በተጨማሪም እጅግ ዘመናዊ የማቀነባበሪያ ማሽን ከቻይና በማስገባት ሰፊ የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየተሠራ እንደሚገኝ ተመላክቷል።

በተመስገን ተስፋዬ