Search

ለበርካታ ከተሞች ምሳሌ የሆነችው አዲስ አበባ

ሰኞ ኅዳር 15, 2018 161

የአፍሪካ መዲና እና 100 በላይ ዲፕሎማቲክ ተቋማት መናኸሪያ የሆነችው አዲስ አበባ፣ ስሟን የሚመጥንና ለነዋሪዎቿ ምቹ የሆነ አካባቢን ለመፍጠር በትኩረት እየሰራች ትገኛለች፡፡

የዘመናዊነት አኗኗርን በመላው ሀገሪቱ በማስፋፋት መሰረተ ልማትን በሁሉም አካባቢዎች በፍጥነት ማዳረስ ወሳኝ ጉዳይ ሆኗል።

በወንዝ ዳርቻዎችም ሆነ በኮሪደር ልማት እየታዩ ያሉ ለውጦች ከተማዋን ከማዘመን ባለፈ፣ የነገውን ትውልድ ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸውን የውጭ ሀገራት ዜጎችም ጭምር ሲናገሩ ተደምጧል።

የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር የፖሊሲ አማካሪ ያሬድ ተሾመ (ዶ/ር) ከኢቲቪ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በአዲስ አበባ እየታዩ ያሉ ለውጦች የፖሊሲ ማዕቀፍ መሻሻል እና የአመራሩ አተያይ ውጤቶች ናቸው ይላሉ።

አክለውም፤ ከተማዋ በፈጣን እድገት እንድትራመድ እና የበርካታ ዓመታት ሥራ በአጭር ጊዜ እንዲከናወን መደረጉንም አንስተዋል።

ፕሮጀክቶቹ በቂ መሰረተ ልማት ከመዘርጋት ባሻገር ሰፊ የሥራ እድል መፍጠራቸውንም አስረድተዋል። በተጨማሪም የኮሪደር ልማቱ ገጠርና ከተማን በእኩል ዓይን ያየና ፍትሐዊ ተደራሽነትን ያሳደገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የከተማ ዲዛይን እና ፕላን አማካሪው ዳንኤል ሊቤሮ (/ር) በበኩላቸው፣ የአዲስ አበባ ውበት ከተፈጥሮአዊ የአየር ንብረቷ ጋር ተዳምሮ ለቱሪስቶች ተመራጭ እንድትሆን አድርጓታል ብለዋል። ይህም በቱሪዝም ዲፕሎማሲ ዘርፍ ትልቅ ለውጥ እያመጣ መሆኑን አመላክተዋል።

በአዲስ አበባ እየታየ ያለው የዘመናዊነት አኗኗር እና የመሰረተ ልማት ተሞክሮ ወደ ሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ለማስፋፋት እንደ ጥሩ ማሳያ እየተወሰደ መሆኑንም ገልፀዋል።

እነዚህን ሥራዎች ወደ ሌሎች ከተሞች በማስፋፋት ዜጎች በየትኛውም አካባቢ የተሟላና ምቹ ኑሮ እንዲኖሩ ማድረግ ይቻላል ሲሉ አብራርተዋል።

በሜሮን ንብረት