Search

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ 4ኛው "መሶብ አንድ ማዕከል" በሚዛን አማን ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ

ረቡዕ ሰኔ 17, 2018 82

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የመንግሥት አገልግሎቶችን ምቹና ተደራሽ በማድረግ፣ ነባራዊ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት 4ኛው "መሶብ አንድ ማዕከል" በሚዛን አማን ከተማ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

ማዕከሉን መርቀው የከፈቱት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ማዕከሉ አገራችን ኢትዮጵያ የጀመረችውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ውጤታማ ለማድረግ ከሚነደፉ ስትራቴጂዎች አንዱ ነው።
በመንግሥት ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶችን ዘመናዊ በማድረግ፣ ኅብረተሰቡ ለሚያነሳቸው የአገልግሎት ጥራት ጥያቄዎች ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት በትኩረት እየተሠራ መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
የማዕከላቱን ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ለአገልግሎት ማብቃት መቻሉ ክልሉ የልማት ፕሮጀክቶችን በብቃትና በጥራት የማከናወን አስተማማኝ አቅም መገንባቱን የሚያሳይ ነው ብለዋል። እነዚህ ማዕከላት ዜጎች ከዲጂታል ቴክኖሎጂ ጋር እንዲላመዱ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥሩም አብራርተዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀብታሙ ካፕትን በበኩላቸው፤ የማዕከሉ መከፈት አገልግሎቶች በቴክኖሎጂ እንዲደገፉ ከማድረጉ ባለፈ፣ የተበታተኑ አሠራሮችን በአንድ ማዕከል በማሰባሰብ የዜጎችን ጊዜ፣ ጉልበትና ሀብት እንደሚቆጥብ አስረድተዋል።
የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየትም፣ የአገልግሎቱ መጀመር በመንግሥትና በሕዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግርና ለመልካም አስተዳደር ችግሮች የተሰጠ አዎንታዊ ምላሽ መሆኑን ገልጸዋል።
በሰለሞን ባረና