Search

በምሥራቅ ቦረና ዞን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ 61 የሸኔ አባላት ወደ ኅብረተሰቡ ተመለሱ

ዓርብ ኅዳር 19, 2018 248

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ቦረና ዞን የሕዝብ እና የመንግሥትን የሰላም ጥሪ የተቀበሉ 61 ሸኔ አባላት በሰላም ወደ ኅብረተሰቡ ተመልሰዋል።
በዞኑ ባለፉት 3 ዓመታት በሰላም እጦት ምክንያት ሕዝብ ከቀዬው ሲፈናቀል እና ሲሰደድ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ሰላምን ለማስፈን በተሠራው ሥራ ሰላም ሰፍኗል።
በዚህም በየጊዜው የተለያዩ የኦነግ ሸኔ አባላት በሰላም እየገቡ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር ገልጿል።
በሰላም ወደ ኅብረተሰቡ የተመለሱት የሸኔ አባላት፣ እርስ በእርስ መጠፋፋት ምንም ፋይዳ እንደሌለው እና ማብቃት እንዳለበት በማመን የሰላም ጥሪውን ተቀብለው መመለሳቸውን ለኢቲቪ ተናግረዋል።
የሐሳብ ልዩነትን በመሣሪያ ለማሸነፍ ያደረጉት ትግል የወንድማማች መገዳደልን ከመፍጠር፣ ኅብረተሰብን ለስቃይ ከመዳረግ እና ንብረት ከማውደም ውጭ ያመጣው ትርፍ አለመኖሩን መረዳታቸውንም ገልጸዋል።
መንግሥትም እያደረገ ያለውን የሰላም ጥሪ አጠናክሮ እንዲቀጥል እና ሌሎች በጫካ የቀሩት ይህንኑ የሰላም ጥሪ ተቀብለው በመመለስ ለሕዝቡ ዕረፍት እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
የምሥራቅ ቦረና ዞን አስተዳዳሪ አቶ አብዱረዛቅ ሁሴን እንደገለጹት ከሁለት ዓመት በፊት በዞን ሙሉ በሙሉ መንቀሳቀስ የማይቻል እንደነበር እና አሁን ላይ በተሠራው ሰላምን የማስፈን ሥራ ሁኔታው መቀየሩን ተናግረዋል።
ለኅብረተሰቡ በተሰጠው ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ በጫካ ያሉ የሸኔ አባላት ከነሙሉ ትጥቃቸው እየገቡ መሆኑ ተገልጿል።
 
በጀማል ነጌሶ