Search

ለቀይ ባሕር ደኅንነት ከኢትዮጵያ የተሻለ ሀገር ማን ነው?

ቅዳሜ ኅዳር 20, 2018 298

ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያስመዘገበችው ያለው ዲፕሎማሲያዊ ስኬት በባለብዙ ወገን ተቋማት ውስጥ ያላትን አቋም ለማጠናከር፣ ቀጣናዊ መረጋጋትን ለማሳደግ፣ የሁለትዮሽ ትብብሮችን ለማጠናከር እና የኢኮኖሚ አጋርነትን በማሳደግ ረገድ ውጤት እያስገኘላት ነው። 

ኢትዮጵያ እንደ አሜሪካ እና ፈረንሣይ ካሉ ወሳኝ ሀገራት ጋር እያደረገችው ያለው ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ ግንኙነቶች የዚህ ነጻብራቅ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሀገራት ጋር የተደረጉት የመከላከያ እና የደኅንነት ትብብሮች የዲፕሎማሲው ፍሬዎች ናቸው። 

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ብሔራዊ ጥቅሟን እና የዜጎቿን ክብር ማዕከል ያደረገ ሲሆን፣ እነዚህን ለማሳካት ደግሞ ኢኮኖሚ አጋርነት እና የትብብር መድረኮች አማራጭ እንደሆኑ ያምናል።

በውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ ቅድሚያ ለጎረቤት የምትሰጠው ኢትዮጵያ እንደ ቱሪዝም፣ ትራንስፖርት እና ኢነርጂ ባሉ ዘርፎች ቀጣናዊ ውህደት ላይ ያተኮረ በርካታ የሁለትዮሽ ስምምነቶችን ከጎረቤት ሀገራት ጋር ተፈራርማለች።

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለይም በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ለሰላም ማስከበር ግንባር ቀደም አስተዋፅዖ የምታደርግ ሀገር መሆኗ ይታወቃል።

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ በቀጣናው እና አፍሪካ ላይ ከፍ ማለት እንቅልፍ የሚነሳቸው ታሪካዊ ጠላቶቿ የሰላም አስተዋጽኦዋን ከግምት ሳያስገቡ ከቀይ ባሕር እንድትርቅ አድርገዋታል፡፡

ቀይ ባሕር ኢትዮጵያ ከወጣችበት በኋላ የሰላም ቀጣና ሳይሆን የስጋት ቀጣና መሆኑን ቀጥሏል፡፡ ቀጣናው የሽብርተኞች መፈልፈያ መሆኑን የቀጠለ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ሩቅ መንገድ መጥተው ቀይ ባሕር ላይ የጦር ሰፈር ያቋቋሙ ሀገራትን ጭንቀት ውስጥ ያስገባ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ለሰላም ቅድሚያ የምትሰጥ እና ሽብርተኝነትን ለመወጋት መስዋዕትነት እየከፈለች ቢሆንም በእነዚህ ሀገራት በኩል የነበረው የትብብር ፍላጎት ተቀዛቅዞ የነበረ ቢሆንም፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በቀጣናው ሰላምን ማስፈን ያለ ኢትዮጵያ አጋርነት እንደማይቻል እየተረዱት መጥተዋል፡፡

በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ፍትሃዊ መሆኑን አምነው ይፋዊ ዕውቅና ሰጥተዋል፡፡ እንደ ፈረንሳይ ያሉ ሀገራት ደግሞ የኢትዮጵያን ባሕር ኃይል እየደገፉ ይገኛሉ፡፡ የአሜሪካ እና ፈረንሣይ ወታደራዊ አዛዦች ሰሞኑን ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅትም ያረጋገጡት ይህንኑ ነው፡፡

አዛዦቹ በፀረ-ሽብርተኝነት፣ በቀጣናዊ መረጋጋት እና በወታደራዊ ድጋፍ ዙሪያ ከጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር ተወያይተዋል፡፡ በውይይታቸውም የኢትዮጵያ በቀይ ባሕር መገኘት ለቀጣናው ሰላም የላቀ አስተዋጽኦ እንዳለው አጽንኦት ሰጥተዋል።

አሜሪካ ኢትዮጵያን በተለይም በአፍሪካ ቀንድ የፀረ-ሽብርተኝነት ጥረቶች ወሳኝ እና አስፈላጊ የደኅንነት አጋር አድርጋ እንደምትመለከታት በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እና ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ጋር የተወያዩት የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ እዝ አዛዥ ጄነራል ዳግቪን አር ኤም አንደርሰን ተናግረዋል።

አዛዡ፣ "ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ ብትገኝ ለቀጣናው ሠላም የበለጠ ትሠራለች" በማለት የኢትዮጵያ በቀይ ባሕር መገኘት ለሰላም ያለውን አስተዋጽኦ ጠቅሰዋል፡፡ 

ፈረንሳይ የፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ሁለት ጉብኝቶችን ጨምሮ በተለያዩ ደረጃዎች በተደረጉ ከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች የ127 ዓመታት ዲፕሎማሲያዊ አጋርነቷን አሳይታለች።

ፕሬዚዳንት ማክሮን ኢትዮጵያ የቀይ ባሕር መውጫ እንድታገኝ ሀገራቸው እንደምትደግፍ በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡

ሁለቱ ሀገራት የመከላከያ ዘርፍን ጨምሮ የተለያዩ የትብብር ማዕቀፍ ያላቸው ሲሆን፣ በመከላከያ ዘርፍ ያለው ስምምነት የኢትዮጵያ ጦር አቅም ግንባታ ሥልጠና እና የሎጂስቲክስ ድጋፍን ያካትታል። ኢትዮጵያ የባሕር ኃይል ስታቋቁም ከፍተኛ ድጋፍ ያደረገችው ፈረንሳይ ነች፡፡

ፈረንሳይ ከወታደራዊ ትብብር ባሻገር በአቪዬሽን ዘርፍ በኤርባስ በኩል የኢትዮጵያ አየር መንገድ ደንበኛ ነች፡፡ እንደ ላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት ያሉ ቅርስ ጥበቃ ላይም የፈረንሳይ አጋርነት የላቀ ነው።

ወታደራዊ ትብብሩ መከካለኛ ምሥራቅ እና እንደ ሞሮኮ ባሉ የሰሜን አፍሪካ ሀገራትንም ያከለለ ነው፡፡ የተባበሩት ዓረብ ኤሜሬቶች ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ጠንካራ ወዳጅነት የመከላከያ ዘርፉን እና የባሕር ሎጂስቲክስን ያጠቃለለ ነው፡፡

ትላንት ደግሞ የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ከኳታር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የመከላከያ ሚኒስትር ጋር ተወያይተዋል።

ሚኒትሮቹ የሁለቱ ሀገራትን ሁለንተናዊ ትብብር ማጠናከር የሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ የተወያዩ ሲሆን፣ በተለይም በመከላከያ ልዩ ልዩ ዘርፎች ያላቸውን ትብብር ለማሳደግ እና ለማጠናከር በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ ተናጋግረዋል፡፡

አሁን የዓለም ዓይኖች ሁሉ ወደ ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ ይህ የዲፕሎማሲ ስኬት የተገኘው ግን በፈተናዎች መካከል በታለፈ ጽናት የተሞላበት ተጋድሎ ነው፡፡

ከሦስት እና አራት ዓመታት በፊት የነበሩ ማዕቀቦች እና ማግለሎች እንዲሁም የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃን ዘመቻን ያየ ማንም ወገን ኢትዮጵያ እዚህ ትደርሳለች ብሎ አያስብም፡፡

ኢትዮጵያ ግን ግልጽ እና ብሔራዊ ጥቅሟን አስቀድሞ ከየትኛው ሀገር ጋር ትብብርን በሚመርጠው የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዋ የብረት አጥሮቹን ሁሉ ሰባብራለች፡፡ ባገኘቻቸው መድረኮች ያስተጋባቻቸው ፍትሃዊ ጥያቄዎቿም ዛሬ ዕውቅና አግኝተዋል፡፡

በለሚ ታደሰ

#Ebc #Ebcdotstream #Ethiopia #RedSea #seaaccess