Search

የኢትዮጵያን ምድረ ቀደምትነት ለዓለም ያበሰረው ግኝት

ቅዳሜ ኅዳር 20, 2018 225

ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት እና የሰው ዘር መገኛ ስለመሆኗ ካረጋገጡ ድንቅ ግኝቶች መካከል የሉሲ ቅሪተ አካል አንደኛው ነው፡፡

የሉሲ ቅሪተ አካል የተገኘው ከ51 ዓመታት በፊት ሕዳር 15 1967 ዓ.ም በአፋር ሀዳር በተሰኘ ቦታ በዚህ ሳምንት ነበር፡፡

ቅሪተ አካሉ በኢትዮጵያ መገኘቱ የሰው ልጅ አመጣጥ ጥናትን የትኩረት መስክ ወደ ኢትዮጵያ ያደረገና ሀገሪቱ እውነተኛ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን ለአለም ያስመሰከረ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን እንደ ማስረጃ የምታቀርበው ሉሲ (ድንቅ ነሸ) የሶስት ነጥብ ሁለት ሚሊዮን አመት ገደማ እድሜ ያስቆጠረች ስለመሆኗ የምርምር ግኝቶቹ አሳይተዋል፡፡

ይህም ግኝት ኢትዮጵያን ከዓለም ልዩ ከማድረጉም ባሻገር እግር ጥሎት ኢትዮጵያ የመጣ ሁሉ ኢትዮጵያ በሰው ዘር መገኛነቷ በመደመም እንዲጎበኛት የሚያደርግ ክስተት ነው፡፡

ድንቅ ነሽ ወይም ሉሲ በመላው ዓለም የምትታወቅበት መጠሪያዋ ሉሲ የተሰኘበት ምክንያት ቅሪተ አካሉን ካገኙት ተመራማሪዎች ጋር የተገናኘ ታሪክ አለው፡፡ 

በዶናልድ ጆንሰን የተመራው የሳይንስ ሊቃውንት ቡድን በወቅቱ ዘቢትልስ በተባሉ ሙዚቀኞች የተቀነቀነውን ታዋቂ "ሉሲ ኢን ዘስካይ ዊዝ ዘዲያመንድ" የተሰኘውን ሙዚቃ እያዳመጡ ቅሪተ አካሉን በማግኘታቸው ያገኙትን ቅሪተ አካልም ሉሲ በማለት ስያሜ በመስጠት ከአለም ጋር አስተዋውቀዋታል፡፡ 

የሉሲ መገኘት ለሌሎች ምርምሮች በር ከፋች በመሆን በርካታ ግኝቶች እንዲከቱሉ ያስቻለ ክስተት ነው፡፡

የሉሲ ቅሪተ አካል የተገኘበት ቦታ የዓለም የአንትሮፖሎጂ ማዕከል እንዲሆን ከማስቻሉም በላይ ይህ ታሪካዊ ስፍራ ለአፋር ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ገፅታ ከፍ አድርጎ በአለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ አድርጎታል፡፡

ይህ የአለምን ቀልብ የሚስበው የሉሲ ቅሪተ አካል ከዚህ ቀደም በአሜሪካ ለእይታ ቀርቦ የነበረ ሲሆን፤ በቅርቡ ደግሞ በቼክ ሪፐብሊክ በፕራግ ብሔራዊ ሙዚየም በነበረው የሁለት ወራት ቆይታ ብቻ ከ 200 ሺህ በላይ ጎብኚዎች እንደጎበኟት መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

ይህም የኢትዮጵያን የሰው ዘር መገኛነት በተግባር ከማሳየቱ በላይ ሌሎች ሐገራዊ ጠቀሜታዎችን ማበርከቱን ቀጥሏል፡፡

በንፍታሌም እንግዳወርቅ

#Ebc #Ebcdotstream #Ethiopia #Lucy