Search

መላው ማኅበረሰብ ለሰላም መስፈን በአንድነት ሊሠራ ይገባል - ርዕሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ

እሑድ ኅዳር 21, 2018 227

የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳደር አረጋ ከበደ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ከደብረ ኤሊያስ ወረዳ ነዋሪዎች ጋር እየተወያዩ ነው።
በውይይቱ ከርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በተጨማሪ ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን ( ዶ/ር)፣ በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የአሥተዳደር ዘርፍ አስተባባሪ አማኑኤል ፈረደ (ዶ/ር) ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ፣ ደብረ ኤሊያስ የሚታወቀው በሰላም ወዳድነቱ እና በአምራችነቱ ነው ብለዋል። ማኅበረሰቡ ለሐይማኖት እና ለዘመናዊ ትምህርት ልዩ ትኩረት የሚሰጥ መኾኑንም ተናግረዋል።
ለሀገር አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሊቃውንት የፈለቁበት፣ ለሀገር የሚበቃ ምርት የሚቀርብበት አካባቢ መኾኑንም ገልጸዋል። ሰላም ወዳድ እና አምራች የሆነው ማኅበረሰብ አሁን ላይ በጸጥታ ችግር ብዙ ዋጋ ከፍሏል ነው ያሉት። በደብረ ኤሊያስ የደረሰው የጸጥታ መታወክ የከፋ እንደነበርም ተናግረዋል።
አውዳሚ የኾነ ሰብዓዊ እና ቁሳዊ ጉዳት እንደደረሰም ገልጸዋል። ንጹሃን በስቃይ እና በጭካኔ የተገደሉበት አካባቢ እንደኾነ ነው የተናገሩት።
አካባቢው ለልማት ትልቅ አቅም ያለው ቢኾንም በጸጥታ ችግር ምክንያት ማልማት ሳይችል ቆይቷል ብለዋል። የደብረ ኤሊያስ አርሶ አደሮች እንዳያመርቱ፣ ምርታቸውን ለገበያ እንዳያቀርቡ እንግልት ሲደረግባቸው እንደቆየም ተናግረዋል።
የትምህርት እና የጤና ተቋማት ተዘግተው መቆየታቸውንም ገልጸው፤ ማኅበረሰብን የሚያዋርድ ተግባር ሲፈጸም እንደነበርም አንስተዋል።
 
ከዚህ በላይ የሚደርስ ግፍ የለም ያሉት ርእሰ መሥተዳድሩ ወጣቶች እና መላው ማኅበረሰብ ለሰላም በአንድነት መነሳት እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል። ሰላም ወዳዱ እና ትርፍ አምራቹ አካባቢ ሲታወክ ዝም ብሎ ማየት እንደማይገባም አስገንዝበዋል።
የአካባቢውን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ማኅበረሰቡ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት እና ከክልሉ የጸጥታ ኃይል ጋር በአንድነት እንዲሠራ ጥሪ አቅርበዋል።
በውይይቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የምሥራቅ ጎጃም ዞን አሥተዳዳሪ ኑርልኝ ብርሃኑ በበኩላቸው፤ ሕዝቡን አንገት ያስደፋ ችግር ገጥሞን ቆይቷል ብለዋል።
በተሠራው ሥራ አሁን ላይ በእጅጉ እየተሻሻለ የመጣ ሰላም ታይቷል ያሉት አሥተዳዳሪው፣ ይሁን እንጂ አሁንም መስተካከል የሚገባቸው በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
የደብረ ኤሊያስ ወረዳ ሕዝብ በከፍተኛ ችግር ውስጥ መቆየቱን አንስተው፤ ወረዳው ከራሱ በላይ ለሌሎች የሚያተርፍ ቢሆንም፤ በራሱ ልጆች እንዳያመርት፣ ልጆቹ እንዳይማሩ ተደርጎ ቆይቷል ብለዋል።
ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጭ እንዲሆኑ፣ መምህራን እንዳያስተምሩ ኾነው መቆየታቸውን ተናግረዋል። በደብረ ኤሊያስ ወረዳ ከአማራ ሕዝብ ባሕልና እሴት ያፈነገጠ ድርጊት ሲፈጸም መቆየቱንም ገልጸዋል።
የአካባቢው ሕዝብ በራሱ ልጆች ሲሰቃይ መክረሙንም ተናግረዋል። የሃይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች እንዳይመክሩ፣ እንዳያስታርቁ በጽንፈኛ ቡድኑ ሲሰቃዩ መኖራቸውንም ተናግረዋል። የአካባቢውን ሰላም በዘላቂነት ማስፈን እንደሚገባም አመላክተዋል።
በዞኑ በርካታ ችግሮች ተፈጥረው ቢቆዩም አሁን ላይ ችግሮችን ለመፍታት እየተሠራ መኾኑን አስገንዝበዋል። የሀገር መከላካያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኃይል ባደረጉት ተጋድሎ የተሻለ ሰላም መፈጠሩንም አንስተዋል።
የሀገር መከላካያ ሠራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ኃይል ላደረጉት አስተዋጽኦም ምስጋና አቅርበዋል።
አስተማማኝ ሰላም እንዲፈጠር የአካባቢው ማኅበረሰብ አሁንም የታጠቁ ኃይሎች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉ ግፊት እንዲያደርግ ጠይቀዋል።
የሰላም አማራጭ ክፍት ነው፤ የሰላም አማራጭን የሚቀበሉትን እንቀበላለን፣ የሰላም አማራጭን በሚገፉት ላይ የሕግ ማስከበር ርምጃው ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ መናገራቸውንም የዘገበው አሚኮ ነው።