Search

ኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷን ካላጠናከረች መልማት አትችልም - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ሰኞ ኅዳር 22, 2018 205

ኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ አንድነቷን ካላጠናከረች ሰላማዊ ልማታዊ ጉዞ ማድረግ እንደማትችል ሁሉም ሰው መገንዘብ እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) አሳሰቡ።

ኢትዮጵያ ያለመችውን ግብ እንድታሳካ የወንድማማችነት እሴትን ማጽናት፣ የሲቪክ ባህልን ማጎልበት እና ቀጣናዊ ትስስርን ማጠናከር አማራጭ የሌለው ቅድመ ሁኔታ መሆኑን ነው የጠቆሙት።

መንግሥት እውነተኛ ፌዴራሊዝም እንዲፀና መሥራት እንዳለበት፣ ለዚህም እያንዳንዱ ክልል በሕግ የተሰጠውን ሥልጣን እና ነጻነት ተጠቅሞ ለሰላም እና ለልማት መሥራት እንደሚገባው ገልጸዋል።

ቋንቋን በተመለከትም የብዝኃ ልሳን ሥርዓት መፈጠር እንዳለበት የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በርካታ ቋንቋዎች በሚነገሩበት ሀገር ውስጥ እነዚያን ማካተት ካልተቻለ ውጤታማ መሆን አይቻልም ብለዋል።

ብዝኃ ማንነቶችን ማቀፍ ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ ገልጸው፣ ኢትዮጵያትክክለኛው መንገድ ላይ እንድትሆን አንደኛው ገዝፎ ሌላው የሚኮሰምንበትን አካሄድ ማስወገድ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ሌላውንውን የሚያቅፍ ወንድማማችነት ሲሰፍን ኢትዮጵያ እንደምትጠቀም ጠቁመው፤ ለዚህም ሌላን እንደ ራስ መመልከት፣ የብሔር ማንነትን እና ሀገራዊ ብሔርተኝነትን ማስታረቅ የሚችል አካታችነት መፈጠር እንዳለበት አስገንዝበዋል።

በመግባባት ቀጣይነት ያላቸው አስታራቂ ተቋማትን መፍጠር ለኢትዮጵያ የሚያስፈልግ ሌላኛው ጉዳይ መሆኑን አንስተው፣ ሕገ መንግሥቱን ጨምሮ የተቋም ግንባታ በጋራ ውይይት እና መግባባት ላይ የተመሠረተ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል።

ከጎረቤት ሀገራት ጋርም አብሮ ማደግን ማዕከል አድርጎ ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ማጠናከር የኢትዮጵያ መንገድ መሆን እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገልጸዋል።

በለሚ ታደሰ

#ebcdotstream #multinationalunity #unityindiversity #abiyahmedali