ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ዛሬ ያለችውን ኢትዮጵያን ከችግር አውጥቶ የሰለጠነች ሀገር ለማድረግ ፍቱን መድኃኒቱ 'መደመር መር' መንግሥት መሆኑን ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ “በመደመር መንግሥት ዕይታ፣ የዘርፎች እመርታ!” በሚል ለብልፅግና ከፍተኛ አመራሮች ሲሰጥ በነበረው ስልጠና ላይ የማጠቃለያ ሀሳብ አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባቀረቡት የማጠቃለያ ሀሳብ፥ በኢትዮጵያ ውስጥ ታሪክ እና የታሪክ ቅሪት ቢኖርም፣ አሁን ላይ የሚታይና የሚጨበጥ በቂ ስልጣኔ አለመኖሩን አንስተዋል።
ታሪክ እንደ ወንዝ ወራጅ ሲሆን፣ ስልጣኔ ግን ድካምና ሥራ የሚጠይቅ ነው ሲሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ስልጣኔን ለማምጣት ሰፊ ጥረት እንደሚጠይቅም አንስተዋል።
ዓባይ ታሪክ ነው፤ ንጋት ግን ስልጣኔ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም ታሪክ በማውራት ብቻ ሳይሆን ታሪክ በመሥራት የተገኘ ድል መሆኑን አስረድተዋል።
እንደዚህ ዓይነት ሥራዎችን ደጋግሞ በመሥራትም ታሪክን ብቻ ሳይሆን ስልጣኔን መጎናጸፍ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ በመደመር ዕሳቤ የሚመራ መንግሥት አይነተኛ መፍትሔ መሆኑን አስረድተዋል።
ቢታኒያ ሲሳይ