Search

ሁሉም አመራር የተሰጠውን ኃላፊነት ለመወጣት የሚያበቃ ስብዕና መላበስ ይገባዋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ሰኞ ኅዳር 22, 2018 161

አመራሮች የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት፣ ብሎም ሌሎችን ለማነሳሳት የሚያበቃ ስብዕና መላበስ ይገባቸዋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
ለብልፅግና ከፍተኛ አመራሮች በተሰጠው ስልጠና ማጠቃለያ ላይ ለውጥ የሚሹ ዋና ዋና ጉዳዮችን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ የማይኮፈስ እና የሚታትር አመራር ማፍራት ለለውጥ ከምንሠራባቸው ጉዳዮች መካከል ቀዳሚው ነው ብለዋል፡፡
የአገልጋይነት ስሜትን ተላብሶ መሥራት እንደሚገባም አመላክተዋል።
በሌላ በኩል ብቁ የሆኑ አመራሮች የሚያንቀሳቅሷቸው ተቋማት፣ ሀገራዊ ግቦችን መሬት ማውረድ በሚያስችል መልኩ እንዲቃኙ ይደረጋል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም በተቋማት ሠራተኞች ላይ የሚታዩ ያልተገቡ ባህሎችን መለወጥ እንደሚገባም አንስተው፤ ሸረኝነት፣ መንደርተኝነት፣ ቅናት፣ አለመሥራት እና አለመትጋት ጎጂ ባህሎች መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለውጥ ከሚሹ ጉዳዮች መካከል የትውልድ ግንባታን ያነሱ ሲሆን፤ ታዳጊዎች የሚታነጹበትን መንገድ እና የሚያዘወትሯቸውን እንቅስቃሴዎች ማጤንና መለወጥ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
ስፖርታዊ እንቅስቃሴን የሚያዘወትሩ፣ ከተፈጥሮ ጋር የተቆራኙ፣ ለንባብ የቀረቡ እና የሀገራቸውን ጸጋ ማስተዋል የቻሉ ዜጎችን ለመፍጠር፤ የተዛቡ የትውልድ ግንባታ ባህሎችን መለወጥ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
እያንዳንዱ ዘርፍ ምን ያህል ሰው ሰራሽ አስተውሎትን በሥራው ተጠቀመ? የሚለውን መመዘን እና አጠቃቀሙን ማሳደግ እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አፅንኦት ሰጥተዋል፡፡
የመደመር መንግሥት ሀገርን ለማሻገር የወሰደውን ኃላፊነት፤ ብዙ በመሥራት እና በመትጋት መወጣት እንደሚገባም አመላክተዋል።
 
አፎሚያ ክበበው