ሀገራዊ ይሁንታ ያልተሰጠበትን፣ የተላለፈበት ሕጋዊ ማስረጃ ያልተገኘለትን የኢትዮጵያ የባሕር በር በሰላማዊ መንገድ መልሶ ማግኘት የትውልድ ጥያቄ ሆኖ ወደፊት መጥቷል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር መሻት ጉዳይ ሲነሳ የውጭ ባዳዎች እና የውስጥ ባንዳዎች ጉዳዩን የመንግሥት ብቻ ለማስመሰል ሲውተረተሩ ዓለም ታዝቧል።
የባሕር በር አማራጭ መሻት የመስፋፋት ሳይሆን በሉዓላዊነት የመቆም፣ የመንግሥትን ሥልጣን ለማራዘም ሳይሆን የታሪክን ስብራት ለማከም የተተለመ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ እንደራሴዎች እንዲሁም በተለያዩ መድረኮች ሲገልጹ ቆይተዋል።
እንዲያም ሆኖ፥ “በዓለም ዙሪያ ካሉ የባሕር በር የሌላቸው 44 ሀገራት፣ የኢትዮጵያን ምን ይለየዋል?” የሚሉ አካላት ስለመኖራቸው በአግራሞት የጠቀሱት ከኢቢሲ ኤፍ.ኤም. አዲስ 97.1 ጋር ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካ ምሁሩ አሊ ሁሴን (ዶ/ር) ናቸው።
ሀገራቱ በታሪክ የባሕር በር አማራጭ ያልነበራቸው በመሆኑ ኢኮኖሚያቸው ከዚያ ጋር ያልተሳሰረ እንደሆነ ዶ/ር አሊ ገልጸው፤ ከፊሉ አሁን ላይ በስምምነት ተጠቃሚ መሆን ስለመቻላቸው ተናግረዋል።
በተጨማሪም ሀገራቱ ያላቸው የሕዝብ ቁጥር ከኢትዮጵያ ጋር ለውድድር የሚቀርብ ያለመሆኑን በማንሳት፤ የነበረንን መጠየቅ ነውር አይደለም ብለዋል።
በሌላ በኩል፥ በኢ-ፍትሐዊ መንገድ ያጣነውን የባሕር በር አማራጭ፤ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ማስመለስ እንችላለን ያሉት በዲላ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር የሆኑት ጌታቸው ታደሰ ናቸው።
ሀገራት ጤናማ ትስስር እዲኖራቸው በማለም እ.አ.አ በ1945 የተፈረመው የተባበሩት መንግሥታት ቻርተር አንቀፅ 2 (ንዑስ አንቀፅ 3) እና አንቀፅ 33 ላይ፥ ሁለት ሀገራት ችግሮቻቸውን በድርድር፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ መፍታት እንዳለባቸው የደነገገ መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢትዮጵያም ይህንኑ እያደረገች ነው ብለዋል።
ይህም በታሪክ፣ በሕግ እና በጂኦግራፊ ጭምር የሚደገፍ መሆኑንም ነው መምህር ጌታቸው የተናገሩት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህን ጉዳይ በተመለከተ በመደመር መጽሐፋቸው፥ “ኢትዮጵያ በምትገነባው ኢኮኖሚ ልክ የሆነ ወደብ ማግኘት አለባት” በማለት ገልጸዋል።
ምክንያቱን ሲያብራሩም፥ “የአካባቢው ሀገሮች የኢኮኖሚ ዕድገት ከኢትዮጵያ ጋር መሳ ለመሳ የሚሄድ ባለመሆኑ፣ የቴክኖሎጂ፣ የሎጂስቲክስ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ እና የብቃት ችግር ሊያጋጥማት ይችላል፤ ስለዚህም፥ ራሷ የምታስተዳድረው፣ በሚያድገው ኢኮኖሚዋ ልክ የምታሰፋው እና የምታዘምነው የወደብ መሠረተ ልማት ያስፈልጋታል” ብለዋል።
“የመደመር መንግሥት እንደ አንድ የኢኮኖሚ መሠረተ ልማት ሊያሳካቸው ከሚተጋቸው አንዱ፣ በኢኮኖሚያዊ ዕድገታችን ልክ የሆነ መሠረተ ልማት እንዲኖር ማድረግ ነው” ሲሉም አስፍረዋል።
በአፎሚያ ክበበው
#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #seaaccess #seaportaccess #outlettothesea #redsea