Search

የምክክር ጉባዔው የሚመክርባቸውን አጀንዳዎች ይፋ ለማድረግ እና ጉባዔውን ለመጥራት ዝግጅት እየተደረገ ነው - ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ

ማክሰኞ ኅዳር 23, 2018 190

ለሀገራዊ ምክክር ቀጣይ ሥራዎች የኃይማኖት ተቋማት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ የበለጠ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ አስታወቁ።

ኮሚሽኑ የምክክር ጉባዔው የሚመክርባቸውን አጀንዳዎች ይፋ ለማድረግ እና ጉባዔውን ለመጥራት ዝግጅቶችን እያደረገ መሆኑ ተገልጿል። 

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ "የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማትና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የላቀ ተሳትፎ ለሀገራዊ ምክክር ውጤታማነት" በሚል መሪ ሃሳብ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

  

የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርዓያ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ኮሚሽኑ ምክክሩ ሁሉን አሳታፊ እና አካታች እንዲሆን ለተሳታፊ ልየታ ሰፊ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን አስታውሰዋል። 

በዚህም የኅብረተሰብ ክፍሎችን፣ የኃይማኖት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን፣ በርካታ ተቋማትና ማህበራትን፣ ታዋቂ ሰዎችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንዲሁም መንግሥትን በተወካዮቻቸው አማካኝነት ማካተትና ማሳተፍ መቻሉን ገልጸዋል። 

ኮሚሽኑ በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይወሰን ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሂደቱ እንዲሳተፉ ጥረት ማድረጉን አንስተዋል።

 

ኮሚሽኑ የምክክር ጉባዔው የሚመክርባቸውን አጀንዳዎች ይፋ ለማድረግ እና ጉባዔውን ለመጥራት የመጨረሻ ምዕራፍ ላይ መድረሱን አስታውቀው፤ ለዚህም ዝግጅቶችን እያደረገ እንደሚገኝ አመልክተዋል። 

ከፍተኛ አመራር አባላት፣ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የካበተ ልምድ ስላላቸው፤ ቀሪ ሥራዎች እንዲሳኩ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ ማቅረባቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ኮሚሽኑ እስከአሁን ያከናወናቸውን ተግባራት ያደነቁት በምክክር መድረኩ የተሳተፉ የኃይማኖት ተቋማት እና የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ኃላፊዎች በበኩላቸው፤ ምክክሩ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ ለስኬታማነቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።

#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #NationalDialogue #ENDC