Search

የባዳ እና የባንዳ አሰላለፍ ለብሔራዊ ጥቅማችን መከበር ትልቅ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል - ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር)

ማክሰኞ ኅዳር 23, 2018 247

ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን ማስከበር ቁልፍ ጉዳይዋ ነው ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዘርፍ ኃላፊ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።

ዶ/ር ቢቂላ ከኤፍኤም አዲስ 97.1 ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ የወል ትርክት የአንድ ሀገር ሕዝብን አብሮነት በማጠናከር የጋራ ሀገራዊ ዓላማን ለመሰነቅ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው እና የታሪክ ሁነቶችን ጭምር የሚያስተሳስር ስለመሆኑ አንስተዋል።

በመሆኑም እንደ ኢትዮጵያውያን ትስስራችንን ይበልጥ የሚያጠናክር እና አንድነታችንን የሚያፀና ታላቅ የጋራ ትርክት መገንባት ያስፈልገናል ሲሉ አመላክተዋል።

የወል ትርክት በመፍጠር ጠንካራ ሀገረ መንግሥትን በጋራ ለመገንባት በምናደርገው ጥረት የባዳ እና የባንዳ አሰላለፍ ለብሔራዊ ጥቅማችን መከበር እና ለኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን መጠናከር ትልቅ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል ብለዋል።

ለአንድ ሀገር ብሔራዊ ጥቅምን ማስከበር ቁልፍ ጉዳይ ነው ያሉት ዶ/ር ቢቂላ፤ ኢትዮጵያ ጥቅሟን ለማስከበር የጀመረችው እንቅስቃሴ በዓለም አቀፍ ሕግ የተደገፈ መብቷ ጭምር ስለመሆኑም ነው የገለጹት።

የብልፅግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር ነብዩ ስሁል በበኩላቸው፥ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም መከበር እንቅፋት ሆኖ የቆየው የባዳ እና የባንዳ አሰላለፍ የተፈጥሮ ሀብቷን እንዳትጠቀም ሲያውካት እንደነበር አንስተዋል።

ኢትዮጵያውያን በጠንካራ ኅብረታቸው የባዕዳንን ተልዕኮ ያነገበውን ይህን አሰላለፍ ቀስ በቀስ በማፍረስ በራስ አቅም ሲያስፈልግም በትብብር ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶችን እውን በማድረግ ላይ መሆናቸውን አክለዋል።

የባንዳ ተልዕኮ ሀገርን ለታሪካዊ ጠላቶች አሳልፎ መስጠትን ግብ ያደረገ በመሆኑ፣ ባንዳዎች የትውልዱን የባሕር በር ጥያቄ ለማጣጣል መሞከራቸው አይገርምም ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ሕልማቸውን ለማምከን ግን በአንድነት መቆም እንደሚገባ አመላክተዋል።

በሜሮን ንብረት

#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #NationalInterest