Search

የጥንት ሥልጣኔን እንደወረት

ሓሙስ ኅዳር 25, 2018 337

ከሜሶፖቶሚ እና ኢትዮጵያ እስከ ግሪክ እና ቻይና ድረስ የተንሰራፋውን የጥንቱ ሥልጣኔ ዛሬም ዓለም እንደማጣቀሻ የሚጠቀመው ነው። ዓለም ሥነ-ጽሑፍ እና ሂሳብን ሲያነሳ ፋርስን፣ ዴሞክራሲን እና ሳይንስን ሲያነሳ ግሪክን መጥቀሱ አይቀርም።

የእነዚህ የጥንት ሥልጣኔዎች በትላንትናው፣ በዛሬው እና በመጪው ትውልድ የሚጠቀሰው መነሻን ለማወቅ እና በዚያ ላይ ሀገርን ለመገንባት ነው።

ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት የነበሩት ሥልጣኔዎች ለአሁኑ እድገት ግብዓት ለቀጣዩን ትውልድ ደግሞ ማስተማሪያ እና መሻገሪያ ድልድዮች ናቸው። ይህ የሚሆነው ታዲያ በእጁ ያለውን አውቆ ለተጠቀመበት ነው።

የእነዚህ የጥንት ሥልጣኔዎች እውነተኛ ሚና የሚታየው በመታሰቢያ ሐውልቶቻቸው ላይ ብቻ ሳይሆን ዘመናዊውን ዓለም በመሥራት ረገድ ባላቸው አበርክቶ ነው። ዘላቂ አስተሳሰብ፣ የሕግ እና የምህንድስና ሥርዓቶች በተግባር ከነባር ሥልጣኔዎች የምንማራቸው ናቸው።

የግሪክ ሥልጣኔ ስፍር ቁጥር ለሌላቸው ዘመናዊ ሪፐብሊኮች እና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቶች የሞራል እና መዋቅራዊ መልህቅ ሆኖ እያገለገለ ያለውን የዲሞክራሲ ጽንሰ ሀሳብን ያስተዋወቀ እንደሆነ ይነገርለታል  

የሮማውያን ቁርጠኝነት ለተደራጀ፣ ሥልታዊ የሕግ ትምህርት በመላው አውሮፓ፣ በላቲን አሜሪካ እና በሌላው ዓለም ሥራ ላይ አየዋለ ላለው የፍትሐ ብሔር ሕግ ሥርዓቶች መሰረት ጥሏል ተብሎም ተተርኮልናል።

እንደ የውል ግዴታዎች እና የጽሑፍ የሕግ ኮድ ሀሳብ ያሉ ፅንሰ-ሀሳቦች በቀጥታ ከሮማውያን ሕግ እንዲሁም እንደ ሃሙራቢ ሕግ ያሉ የሞሶፖቶሚያ ፈጠራዎች ለዓለም ሥልጣኔ መሰረት እንደሆኑ ይጠቀሳል።

በሕግ፣ በሒሳብ እና በምህንድስና ረገድ ያበቡ ጥንታዊ ስኬቶች በዘመናዊ የቴክኖሎጂ እድገት ላይ ያላቸው አስተዋጽኦ ታሪካቸውን ከመማር ያለፈ ከፍተኛ ሚና አለው።  

የሞሶፖቶሚያ ሥልጣኔ በሥነ ፈለክ ምርምር የተራቀቀ እና ሒሳብን ያዳበረው ከዛሬ ሺህ ዓመታት በፊት ሲሆን፣ ዛሬም ሒሳብ እና ሥነ-ፈለክ የዓለም የምርምር ቁንጮዎች ናቸው።

ኮምፓስ፣ የወረቀት ሥራ እና የህትመት ቴክኒኮችን ጨምሮ የቻይና ፈጠራዎች ግንኙነትን እና ዓለም አቀፋዊ ልውውጥን አብዮት አስነስተዋል። ይህም ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ ለመጣው የሳይንስ አብዮት መሰረት ጥሏል። ቻይናም ያን መሰረቷን መንደርደሪያ አድርጋ አንድ ወቅት የገጠማትን ስብራት ጠግናበታለች።

የሚቀጥለው ትውልድ መሐንዲሶች፣ የከተማ እቅድ አውጪዎች፣ የሥነ-ፈለክ ተመራማሪዎች እና የሌሎች ዘርፎች ሳይንቲስቶች በእነዚህ የጥንት ሥልጣኔ መሰረቶች ላይ ቆመው የትውልዳቸውን አሻራ ማሳረፋቸውን ይቀጥላሉ።

የጥንት ሥልጣኔዎች ሚና ታሪክን ከማነብነብ እና ከቱሪዝም ጠቀሜታቸው በላይ የትውልድ ቅብብሎሽ ድልድዮች ናቸው። ትውልድን ከተኛበት የሚያነቁ የብርታት ደወሎችም ናቸው። በዓለም ላይ ካሉ ሀገራት የጥንት ሥልጣኔዋን እንደ መስፈንጠሪያ የተጠቀመ ሀገር ያለ አይመስልም። እርግጥ እዚህ ላይ እንደ ቻይና እና ጃፓን ያሉ ሀገራት ወዲህ ደግሞ ቱርክዬ ግን የቀድሞ ሥልጣኔያቸውን ለዛሬው እድገታቸው መስፈንጠሪያ ሳያደርጉት አልቀሩም። 

ኢትዮጵያ እና ሥልጣኔ

ዓለም ላይ ካሉት ቀዳሚ ሀገራት መካከል የምትገኘው እና የሰው ዘር መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ ተቆጥረው የማያልቁ የጥንታዊ ሥልጣኔዎች ባለቤት ነች።

ከክርስቶስ ልደት በፊት 900 ዓመተ ዓለም አካባቢ ጀምሮ የነበረው የዳኣማት ሥልጣኔ ከኢትዮጵያ የሦስት ሺህ ዓመታት ሥልጣኔዎች መካከል ይጠቀሳል። ዛሬም በአካል የሚገኙት የየሓ ቤተ መቅደሶች እና ቤተ መንግሥት የዚህ ሥልጣኔ ምስክሮች ናቸው። ያኔ ኢትዮጵያ ባሕር ተሻግራ ዓለም አቀፍ ንግድ የምታካሄድ ሀገርም ነበረች።

ከየሓ ሥልጣኔ ቀጥሎ የመጣው የአክሱማውያን ሥልጣኔ ዛሬም ብዙዎች ያልፈቷቸውን ምስጢሮች ይዞ ቀጥሏል። የአክሱማውያን መንግሥት ሮም፣ ፋርስ እና ቻይናን ጨምሮ በወቅቱ በዓለም ላይ ከነበሩት አራት ኃያላን መንግሥታት መካከል አንዱ ነበር። የአክሱማውያን ዘመን ኢትዮጵያ በንግድ፣ በሥነ-ሕንጻ፣ በሥነ-ፈለክ እና በሌሎች ሥልጣኔዎች ከፍተኛ ደረጃ የደረሰችበት ዘመን ነበር።

የዛግዌ ሥርዎ መንግሥት ሌላው ኢትዮጵያ በሥልጣኔ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰችበት ዘመን ነበር። የአስተዳደር እና የሥነ-ሕንጻ አሻራዎቹ ደግሞ የዛግዌ ሥርዎ መንግሥት ሥልጣኔ ምስክሮች ናቸው።

የጎንደር እና አካባቢው ሥልጣኔም ሌላኛው የኢትጵያ ሥልጣኔ ከፍታ ዘመን ማሳያዎች ናቸው። በየአካባቢው የተሠሩ አብያተ መንግሥታት፣ ድልድዮች እና የውጭ ግንኙነት ፖሊሲዎች የጎንደርን ከፍታ የሚመሰክሩ እና ዓለምን ይኸን አረጋግጦ ዕውቅና የሰጣቸው ናቸው።

የገዳ ሥርዓት የእነ ግሪክ የዴሞክራሲ ጽንሰ-ሀሳብ ሳይወለድ በተግባር የነበረ ዴሞክራሲያዊ የአስተዳደር ሥርዓት ነው። በገዳ ሥርዓት የሥልጣን ዘመን የተገደበበት፣ መሪ ገና ሲወለድ ጀምሮ የሚዘጋጅበት፣ እያንዳንዱ የሥርዓቱ አባል በየእርከኑ የሚያበረክተው ማኅበረሰባዊ አስተዋጽኦ በዝርዝር የተቀመጠበት የአስተዳደር ሥርዓት ነው።

ኢትዮጵያ ታዲያ ሥልጣኔዋን የት አደረሰችው?

ዛሬ በዓለም ላይ የሥልጣኔ መነሻ ተብለው የሚነገርላቸው ሀገራት የታላቅነታቸው ምስጢር መሰረታቸውን አለመልቀቃቸው ነው። መሰረታቸው ላይ ገንብተው በማሳደግ ነው ሥልጣኔያቸውን የኩራታቸው ምንጭ ያደረጉት። ሮም "በአንድ ቀን አልተገነባችም" የሚል አባባል እስከመፍጠር የደረሱት ጣሊያናውያን በታሪካቸው ውስጥ ከገጠማቸው ፈተና የወጡት ያንን ሥልጣኔያቸውን መንደርደሪያ በማድረግ ነው። ዓለም ላይ የሁሉም ነገር ጀማሪ እነሱ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ግሪኮች የፈጠሩትን የጥንት ሥልጣኔ ትርክታቸውን ተጠቅመው ውብ ሀገር ሠርተውበታል።

ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ አንዱን ጥሎ ሌላ የመጀመር፣ ያለፈውን ደምስሶ አንዲስ የመገንባት አባዜ ሥልጣኔዎቿን እንደ መስፈንጠሪያ እንዳትጠቀም አድርጓት ቆይቷል። የአክሱምን ያህል ያል ሥልጣኔ የነበረበት ሀገር ለምን ከመጨረሻዎቹ ተርታ ተሰለፈ? እነ ላሊበላን የሠሩ ጥበበኛ እጆች ለምን ለማኝ ሆኑ? ከዓለም ጥቂት ኃያላን መካከል የነበረችው ኢትዮጵያ ለምን ውራ ሆና ቀረች? የእነዚህ ጥያቄዎች ዋነኛ ምላሽ ሥልጣኔዋን እንመንደርደሪያ አለመጠቀሟ መሆኑን ብንናገር ብዙም ከእውነት አልራቅንም።

ጥንታዊ ሥልጣኔ በመደመር መንግሥት እይታ

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) እሳቤ የሆነው መደመር ከትላንቱ እሴት ጠቃሚውን መውሰድ እና አሳምሮ ለትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ በጽንሰ-ሀሳብም በተግባርም አረጋግጧል።

ሀገር የሚገነባው በትውልድ ቅብብሎሽ እንደመሆኑ ቀድሞ የተጀመሩ ሥራዎችን በማስቀጠል የተበላሹትን አክሞ በማስተካከል ወረት ይዞ ሀገር መገንባት አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በተግባር እየተገለጠ ነው። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ነው። ግንባታው ተጀምሮ በብዙ ውስብስብ ችግሮች ውስጥ እያለፈ የነበረው ህዳሴ መተው ቀላሉ ሥራ ቢሆንም እየደመሰሱ የመቅዳት አባዜን ማከሚያ ትክክለኛ ቦታም ማድረግ ተችሏል። ከውስብስቡ ችግር ውስጥ አላቆ ለስኬት በማብቃት የኢትዮጵያን የስኬት ምስጢር እንዲጀመር ምክንያትም ጭምር ሆኗል።  

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለብልፅግና አመራሮች በሰጡት ሥልጠናም ዳግም ያረጋገጡትም ይኸንኑ ነው። "ታሪክ እንደወንዝ ወራጅ ነው" የሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በወንዝ የተመሰለውን ታሪክ ጠቃሚ ለማድረግ በድካም እና በሥራ መቀየስ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል። ለዚህም ታሪክ በሆነው ዓባይ ላይ የተሠራው ንጋት የዚህ ዘመን ትውልድ የሠራው የሥልጣኔ ምሳሌ እንደሆነ በማሳያነት አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ ቀደምት እንደነበረች ነገር ግን በሆነ አዙሪት ውስጥ ገብታ እንደተንሸራተተች ጠቅሰው፣ አሁን ግን እነዚያን ድንቅ ሥልጣኔዎቿን እንደ ማነቃቂያ ተጠቅማ መነሳት እንዳለባት አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ ዛሬም እነዚያ እንደ ሀገር አስተሳስረው ያቋዩአትን እና የጥንታዊ መንግሥት ሥርዓት ባለቤት ያደረጓትን ሥልጣኔዎቿን እንደ መስፈንጠሪያ ከተጠቀመች ወደ ከፍታዋ መመለስ እንደምትችል ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያወሱት።

በመሆኑም ሥልጣኔዋን ማነቃቂያ እና መስፈንጠሪያ አድርጋ በብዙ ወደኋላ ከቀረችበት ቦታ ለመዝለል ልትጠቀምበት ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሳሰቡት።

በለሚ ታደሰ