ኢትዮጵያ እንድትበታተን ከሚፈልጉ ኃይሎች ጋር የሚደረግ ግንኙነት አጥፊ እንጂ የሕዝብ ጥያቄ ሊሆን አይችልም ሲሉ ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ ገለጹ፡፡
በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) መካከል የሰላም ስምምነት ተፈርሟል፡፡

የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅትን በመወከል ስምምነቱን የፈረሙት ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በጦርነት ተጀምሮ በጦርነት ያለቀ ታሪክ የለም፣ ሕዝቡም ውጊያውን ከዚህ በላይ መሸከም አይችልም ብለዋል።
የትኛውም ችግር በጦርነት እንደማይመለስ ጠቁመው፤ ምንም አይነት የሕዝብ ጥያቄ አለኝ ቢባል እንኳ ከታሪካዊ ጠላቶች ጋር የሚደረግ ትብብር ለሀገር አንድነት ስጋት እንጂ መፍትሔ ሊሆን እንደማይቻልም አመላክተዋል።
በተለያዩ አካባቢዎች ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ቡድኖች በጥፋት መንገድ የሚመለስ የሕዝብ ጥያቄ እንደሌለ በመረዳት፤ የሰላምን መንገድ መከተልና ወደ ውይይት በመምጣት ችግሮቻቸውን በንግግር እንዲፈቱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በአማራ ክልል ለሁለት ዓመታት ሲደረግ የነበረው የግጭት አዙሪት እንዲቆም ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ ለነበሩት የአፍሪካ ሕብረት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
በሁለቱ ወገኖች ስምምነት ላይ በአደራዳሪነት የአፍሪካ ሕብረት እና ኢጋድ ተሳትፈዋል።
በሀይማኖት ከበደ